የዶክተር ነጋሶን ጤንነት ለመታደግ 8 ሺህ ዩሮ ያስፈልጋል ተባለ

ሰኔ ፲፱ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የቀድሞው  የአገሪቱ ፕሬዝዳንት እና የአሁኑ የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ  እግራቸው ላይ በተከሰተ የደም ዝውውር ችግር በአደገኛ የጤና ችግር ላይ እንደሚገኙ ተገለፀ።

የዶክተሮችን የምርምር ውጤት በመጥቀስ ፍኖተ-ነፃነት እንደዘገበው፤ ዶክተር ነጋሶ በአስቸኳይ ኦፕራሲዮን ካልተደረጉ እግራቸው ሊቆረጥ ይችላል።

በመሆኑም የ ኢትዮጵያ ህዝብ የዶክተር ነጋሶን ጤንነት ይታደግ ዘንድ አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ህዝባዊ ጥሪ አቅርቧል።

ዶክተር ነጋሶ  ቀደም ሲልም ረጅም መንገድ ሲጓዙ እግራቸውን ያማቸው እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን፤ ይህ ህመም ጀርመን ሀገር ከሄዱ በኋላ ተባብሶ ወደከፋ ደረጃ  መድረሱ ታውቋል።

እዚያው ጀርመን ሀገር ሀኪም ቤት በመሄድ ከተመረመሩ በኋላ እንዳረጋገጡት ፤በአስቸኳይ ኦፕራሲዮን ተደርገው ህክምና ካላገኙ እና  ወደ እግራቸው የሚሄደውና የተዘጋው የደም ዝውውር ካልተስተካከለ በስተቀር፤ እግራቸው  ወደ በድንነት እንደሚቀየርና ወደ መቆረጥ እንደሚያመራ በሐኪሞች ተገልጾላቸዋል።

የፓርቲው  የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር ኃይሉ አርአያ  እንደተናገሩት  ዶክተር ነጋሶ ለኦፕራሲዮኑ በጠቅላላ 8 ሺ ዩሮ የተጠየቁ ሲሆን ፤ይሄን ለመክፈል የሚያስችል አቅም የላቸውም፡፡

ለ6 ዓመት ኢትዮጵያን በፕሬዝዳንትነት ያገለገሉት ዶክተር ነጋሶ ከገዥው ፓርቲ ጋር የ አቋም ልዩነት በማሳየታቸው ምክንያት የጡረታ መብታቸው እንዳይከበርላቸው መደረጉ ይታወቃል።

የቀድሞው  ያገሪቱ ርዕሰ ብሔር በተለይ ኢህአዴግን በአደባባይ ፦”በቃኝ አልፈልግም” ብለው በመናገር ከለቀቁ በኋላ የተለያዩ የማጥቃት ዘመቻዎች ተከፍተውባቸው መቆየቱን ያስታወሱት ዶክተር ሀይሉ፤ በዚህም ሳቢያ  ህይወታቸውን በትንሽ የፓርላማ ጡረታ ብቻ ለመግፋት መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡

“የእኚህን የህዝብ ቅን አገልጋይ ህይወት ለመታደግ የኢትዮጵያ ህዝብ የአቅሙን በማዋጣትና እንዲረባረብ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን››ሲሉም ዶክተር ሀይሉ  በፓርቲያቸው ስም ህዝባዊ ጥሪ አቅርበዋል።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ፤ከሌሎች ባለስልጣናት በተለየ መልኩ  የቀድሞው የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ  ምንም አይነት ንብረትና ሀብት የላቸውም።

ዶ/ር ነጋሶን ለመርዳት የሚፈልጉ ሁሉ ፤በንብ ባንክ ዑራኤል ቅርንጫፍ የሒሳብ ቁጥር 9095  ድጋፋቸውን ማስገባት እንደሚችሉ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊው ገልጸዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide