መንግስት፤ የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅን ከአልሸባብ ጋር በማገናኘት ለመወንጀል የሸረበው ድራማ ተጋለጠ

ሰኔ ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የአቶ መለስ መንግስት ባለሟሎች  ማንንም ሊያሳምን በማይችል ደረጃ ፍትህ ጋዜጣን ከአልሸባብ ጋር ግንኙነት እንዳለው በማስመሰል የፈበረኩትን አስቂኝ ድራማ ያጋለጠው፤  የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ነው።

“ፍትህን እና አልሸባብን  ምን አገናኛቸው?” በሚል ርዕስ ጋዜጠኛ ተመስገን ባስነበበው ጽሁፍ፤ አዲስ ዘመንና በተመሳሳይ መስመር የተሰለፉት እነ አይጋ ፎረም፣ዋልታ እና ዛሚ፤ በፍትህ ጋዜጣ ላይ “አርማጌዶን” ወይም “የፍፃሜ ጦርነት” ማወጃቸውን ገልጿል።

ለነዚህ ሚዲያዎች የሀሰት ውንጀላ ለረዥም ጊዜ  ምላሽ መስጠት ባለመፈለጉ ፦” ውሾቹ ይጮኻሉ…”በሚል ብሂል ነገሩን ችላ ብሎት እንደነበር ያወሳው ጋዜጠኛ ተመስገን፤ አሁን ግን ውንጀላው አደገኛ አዝማሚያ እየያዘ በመምጣቱ  ምላሽ ለመስጠት መገደዱን ጠቅሷል።

እንደ ተመስገን  ጽሁፍ፤አዲስ ዘመንና እነ አይጋ  በሁለት ወራት ውስጥ ብቻ ፦‹‹ተነስ ያሉት እምቢ ቢል በ‹ጊዜ ለኩሉ…››፣‹‹የገደል ጫፍ ላይ ሩጫ››፣ ‹‹በአዲስ መልክ ሥራ ጀምረናል!› ሌላው የመድረክ የፕሮፓጋንዳ ‹ጭብጥ› ይሆን እንዴ?››፣ ‹‹ፍትህና አምደኞቿን በጨረፍታ›› ፣ ‹‹የጨለማው ዘማሪዎች መናኸሪያና ደቀ-መዝሙሮቹ›› ‹‹የዋህ ነፍሰ ገዳይ››፣ ‹‹ለአመጽ እና ብጥብጥ የሚመች ፕሬስ ነፃ አይደለም››፣ ‹‹አንቀጽ 29፣ የፕሬስ ቀንና ማተሚያ ድርጅት››፣ ‹‹በደም የተፃፈው ህገ-መንግስት ያደፈው በማን ነው?››፣ ግራ የተጋባው የፖሊሲ ሰነድ ‹ትንተና›…›› በሚሉ ርዕሶች  በፍትህና ባልደረቦቿ ላይ ያነጣጠሩ አስራ ስምንት  ጽሁፎችን አትመዋል።

የሁሉም ጽሁፎች ይዘት፤  “ፍትህ በአሸባሪ ድርጅቶች እና በኤርትራ መንግስት በገንዘብ ይደገፋል” በሚል መደምደሚያ የሚያልቁ  መሆናቸውን የጠቀሰው ተመስገን፤ ለዚህም  እንደምክንያት የሚያቀርቡት ጋዜጣዋ ያለ በቂ ማስታወቂያ እስከአሁን በህትመት መቆየቷን  እንደሆነ ፤ የነ አዲስ ዘመንን ጽሁፎችን በዋቢነት በመጥቀስ አሳይቷል።

‹‹ፍትህ ያለማስታወቂያ እስከዛሬ ድረስ በገበያ ላይ የቆየችው፤ በአለም አቀፍ አሸባሪ ድርጅቶች፣ በኤርትራ መንግስት፣ በግንቦት 7፣ በኦብነግ፣ በኦነግ፣ በአክራሪ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራ… ድጋፍ ነው››  የሚል ፕሮፓጋንዳ ነው እነ ዘመን ሲያሰራጩ የከረሙት።

ይሁንና  ባለፈው ሳምንት የደረሰው አንድ መረጃ ፤ይህ ውንጀላ አንድ ደረጃ ጨምሮ መልኩን እየለወጠና ነገሮች እየተበላሹ መምጣታቸውን የሚያመላክት እንደሆነ፤ ጋዜጠኛ ተመስገን አመልክቷል።

ባለፈው ሳምንት ከአልሸባብ እንደተላከ የሚገልጽ ፤ሆኖም የመልዕክቱ ይዘትና ቋንቋ እነ አዲስ ዘመን ፦ፍትህን ሲወነጅሉ ከኖሩበት የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ጋር ተመሣሳይ  የሆነ ደብዳቤ እንደደረሰው ፤ጋዜጠኛ ተመስገን ይፋ አድርጓል።

“በዚህ መልእክት ላይ ‹‹ላኪ›› ተብሎ የተቀመጠው እንደተለመደው ‹‹አዲስ ዘመን›› ሳይሆን ‹‹አልሸባብ›› የተባለው የሶማሊያ አሸባሪ ድርጅት ነው” ያለው ተመስገን፤ የመልእክቱ ይዘት ግን አዲስ ዘመን በሚያዚያ እና በግንቦት ወር ፍትህን ሲወነጅልበት ከነበረው በምንም  እንደማይለያ እና ተመሳስሎአቸው ቃል በቃል እንደሆነ አመላክቷል።

በአልሸባብ ስም በእግሊዝኛ ቋንቋ   ለአቶ ተመስገን የተፃፈው ደብዳቤም እንደሚከተለው ነው፦

“ (ለአቶ ተመስገን ደሳለኝ

 የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ

 ኢትዮጵያ

 እንደሚታወሰው አልሸባብ በኢትዮጵያ፣ በሱማሌላንድ፣ በኬንያ እና በኡጋንዳ የፕሮፓጋንዳ ስራ እንድሰራ በሚስጥር መድቦኛል። ይህንኑ ግዴታዬን ለመወጣት በአንተ ጋዜጣ ላይ የኢትዮጵያ መንግስትን፣ የኢትዮጵያ ህዝብን እና የአሜሪካንን መንግስት ጥቅም የሚጎዳ የቅስቀሳ ፅሁፎች ይታተሙ ዘንድ አቶ ማሙሽ ሴንጢ በተባለው ተወካይህ አማካኝነት ኤርትራ ውስጥ ተስማምተን ነበር። እንደምታውቀውም 30 ተከታታይ እትምች 24,000 የአሜሪካን ዶላር ከፍለንሃል። አሁን ግን አልሸባብ ዕቅዶቹን ለመፈፀም የስልት ለውጥ አድርጓል። ስለዚህም 11,200 የአሜሪካን ዶላር የሚሆነውን 14 እትሞች ክፍያ ለአልሸባብ እንዲመለስ እንፈልጋለን። ይህንን ገንዘብ ለድርጅታችን ትመልሳለህ ብለንም እናምናለን። ነገረ ግን ምናልባት ይህ ሁኔታ በሰዓቱ ባይሳካ በድርጅቱ ህግ መሰረት በአቶ ማሙሽ ሴንጢና በአንተ ህይወት ዋጋ ትከፍላለህ።

 አልሸባብ ያሸንፋል።

 አህመዲን ናስር)”

ይህ መልዕክት የተላከው ከአልሸባብ-ለእኔ መሆኑ ነው “  ያለው ተመስገን፤ የዚህ መልዕክት ጭብጥ ሚያዚያ 2/2004 ዓ.ም በወጣው‹‹ፍትህና አምደኞቹን በጨረፍታ-ክፍል ሶስት›› በሚል ርዕስ ከታተመው ጋዜጣ  ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ አመልክቷል።

በተጠቀሰው ቀን በታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ የወጣው ጽሁፍ ውስጥ፡- ‹‹ከምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ለተቀመጠችው ሀገራችን አልሸባብን ጨምሮ ሌሎችን ከውስጥም ከውጭም የፀረ-ሰላም ኃይሎች ያሰባሰበው፤ የኢሳያስ አፈወርቄ መንግስት ናቅፋ፤ እስከፍትህ ቢሮና አምደኞች ኪስ አይደርስም ማለት አይቻልም፤ ይህ ባይሆን እመኛለሁ፤ እኔ ግን በበኩሌ ጠረጠርኩ፤ በርካታ ማሳያዎች አሉኛ›› የሚል  እንደሚገኝበት ተመስገን አሳይቷል።

እንደ ተመስገን ገለፃ፤ይህን ደብዳቤ ፦ እነ አዲስ  ዘመን ፍትህን ሲወነጅሉባቸው ከነበሩት  ጽሆፎች የሚለየው፤ የተፃፈበት ቋንቋ ብቻ ነው።

“ያለው ልዩነት፤ የአዲስ ዘመን በአማርኛ ቋንቋ፣ አልሸባብ ላከው የተባለው  ደግሞ በእንግሊዝኛ ቋንቋ መፃፉ ብቻ ነው”ብላል-ጋዜጠኛ ተመስገን።

“ ከዚህ የሀሰት መወንጀያ ለማሳያ ያህል እነዚህን የመዘዝኩት በሀገራችን ዜጎች ምን ያህል በሀሰተኛ ማስረጃ እና ምስክር ለእስር እየተዳረጉ እንደሆነ እንድትረዱት ነው” በማለትም፦ “የቃሊቲው መንግስት “በተሰኘው የሢሳይ አጌና መፃህፍት ላይ <በፍርድ ቤት በሚቀርቡ የሀሰት ማስረጃዎች ፤አቃብያነ ህጎች ሳይቀሩ የሚያፍሩባቸው አጋጣሚዎች እንደነበሩ> መጠቀሱን አውስቷል።

“ በእነዚህ፦ በመንግስታዊው ጋዜጣ እና በአፍቃሬ ኢህአዴግ ድረ-ገጾች ከወጡት ቁጥራቸው የበዛ ፅሁፎች መሀከል በጥቂቱ ለማሳያነት ያህል የጠቀስኳቸው ውንጀላዎች፤ በአምባገነዊ ስርዓት ውስጥ ያለውን የነፃ ጋዜጠኝነት ፈተና በበቂ የሚያሳዩ ይመስለኛል” ያለው ተመስገን፤ “ ስርዓቱ እዚህ ድረስ ወርዶ ለመወንጀል እየሞከረ ያለው፦ ሀገራችንን ጥለን እንድንሄድ አልያም ራሳችንን በዝምታ እንድንሸብብ ከሆነ፤ የሚሰማ ካለ አቋማችንን በተደጋጋሚ ማሳወቃችንን ብቻ አስታውሶ ከማለፍ ውጭ አማራጭ የለውም”ብሏል።

ተመስገን  ጽሁፉን ሲያጠቃልልም፦ “የሃገሪቱ ህገ-መንግስት ላይ የሰፈሩ የዜግነት ነፃነት አክባሪ ዕሴቶችን አምነን ስለሀገራችን በዋተትን፣ ለተጎዱና ለተገፉት ወገኖቻችን ባበርን፣ የህዝባችን ያለስጋት በነፃነት የመኖር መሻት ይተገበር ዘንድ በብዕሮቻችን በቃተትን፤ በማንኛውም መልክ ሊመጣ የሚችል አደጋ ካለ ፤ከመቀበል ውጪ ሌላ ምርጫ የለንም። ምክንያቱም ሀገራችን፤ ኢትዮጵያ ብቻ ናትና” ብሏል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide