ወይዘሮ አዜብ መስፍን በሙስና መሬት መውሰዳቸውን ያጋለጠ ሠራተኛ ታሰረ

ግንቦት ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የማዘጋጃ ቤቱ ሠራተኛ  በቅጽል ስማቸው የሙስና እናት ተብለው የሚጠሩትን ወይዘሮ አዜብን ያጋለጠው፤ በቡራዮ ከተማ በተካሄደ እና በአዲስ አበባ ከንቲባ በኩማ ደመቅሳ በተመራ የግምገማ መድረክ ላይ ነው።

የቡራዮ ነዋሪዎች ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል እንደተናገሩት፤ የግምገማው መድረክ በቡራዩ አካባቢ የመሬት ቅርምት ተፈጽሟል፤ በመንግስትና በህዝብ መሬት፤ ግለሰቦች አላግባብ በልጽገዋል፤ ከመሬት ጋር በተያያዘ  ከፍተኛ ሙስና ተፈጽሟል” ተብሎ ነበር።

እንደ ነዋሪዎቹ ገለፃ፤የግምገማውን መድረክ የሚመሩት ባለስልጣኖች የስብሰባውን አቅጣጫ ወደሚፈልጉት መንገድ በመውሰድ ተሰብሳቢው ፦ከቁጥር ወደማይገቡ የአካባቢው ሀላፊዎች ላይ ብቻ ጣቱን እንዲቀስር እንዲያጋልጥ ግፊት ሲያደርጉ ተስተውለዋል።

ይህንን የተገነዘበው አቶ ኃይሉ ንጉሴ የተባሉ የማዘጋጃ ቤቱ የፋይናንስ ሠራተኛ ከወንበራቸው በመነሳት፦“ትኩረታችሁን ለምን በትንንሾቹ ብቻ ታደርጋላችሁ? ሙስናን በቁርጠኝነት የምትታገሉ ከሆነ ወደ ላይም ተመልከቱ፡፡ በዚህ በከተማችን  ውስጥ ወ/ሮ አዜብ መስፍን በወንድማቸው ስም መሬት ወስደዋል፡፡እሱ  ለምን አይጣራም? ለምን እሳቸውስ አይጠየቁም?” በማለት  ተናግሯል።

የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የተቋቋመበትን 10ኛ ዓመት ከወራት በፊት በሂልተን ሆቴል ሲያከብር ስለኮሚሽኑ ያለፈ የስራ ሂደት ጥናት ያቀረቡ አንድ የ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁር፦”ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ባለፈ ጉዞው ካስቀጣቸው ከ 500 በላይ ሰዎች አንድም ከፍተኛ ባለስልጣን እንደማይገኝበት በመጥቀስ፦”ኮሚሽኑ ከፍተኛ የመንግስት ተሿሚዎችን ይፈራል”ማለታቸው ይታወሳል።

ሰሞኑን በቡራዮ ከተማ በተካሄደው ግምገማ ላይ የማዘጋጃ ቤቱ ሠራተኛ  ንግግር ያረጋገጠውም ይህንኑ እውነታ ነው።

“ስብሰባው በከተማችን ከመሬት ጋር ተያይዞ የተፈፀመን ሙስናን  ለማጋለጥ ከሆነ፤ ወይዘሮ አዜብም በወንድማቸው ስም በከተማችን መሬት ወስደዋል። እርሳቸውም ይጠየቁ”ነው ያሉት-አቶ ሀይሉ ንጉሴ።

ይሁንና በወቅቱ ስብሰባውን የሚመሩት ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ፦ “ጥቆማው አንድና አንድ ነው፡፡ ጥቆማው በማስረጃ መረጋገጥ አለበት፡፡ ዝም ብሎ መጠቆም አይደለም፡፡” በማለት ጥቆማውን  እንዳጣጣሉት ተሰብሳቢዎቹ ተናግረዋል።

 

“ይህ ሲገርመን ሰሞኑን ወይዘሮ አዜብን ያጋለጡት አቶ ሀይሉ  በሙስና ትፈለጋለህ” ተብለው ታስረዋል ያሉት የቡራዮ ነዋሪዎች፤

ይህም መንግስት  ሙስናን ለመዋጋት ያለውን ቁርጠኝነትና ጥያቄ ውስጥ የሚከት ከመሆኑም በላይ በመንግስት ላይ ያለንን እምነት ሸርሽሮታል “ብለዋል።

በርካታ ሰዎች  ለአቶ መለስ ፓርላማ በቀረቡ ቁጥር ፦” የመንግስት ሌቦች” እያሉ የሚናገሩት ፃድቅ መስሎ በመታዬት የራስን ጉድ ለመሸፈን ነው” ሲሉ ይደመጣሉ።

ሰው የሚበላው አጥቶ በተቸገረበት ወቅት ለአንድ ጊዜ  የጌጣጌጥ እና የ አልባሳት ግዥ ሚሊዮን ብሮችን  እንደሚያወጡ በውጪ ጋዜጦች የተዘገበባቸው  ወ/ሮ አዜብ መስፍን ፤በአሁኑ ጊዜ በአገራችን በሙስና ከፍተኛ ሀብት አፍርተዋል ተብሎ ከሚታሙት ግለሰቦች ውስጥ የመጀመሪያዋ ናቸው።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide