በዩክሬን የፓርላማ አባላት ተደባደቡ

ግንቦት ፳፩ (ሃያ አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በዩክሬን ምሥራቃዊ ግዛት በፍርድ ቤቶች፣ በሆስፒታሎች እና  በመንግስታዊ ተቋማት ውስጥ የሩሲያን ቋንቋ ለመጠቀም በወጣው ረቂቅ አዋጅ ሳቢያ የፓርላማ አባላት ተደባደቡ።

እንደ አሶሲየትድ ፕሬስ ዘገባ፤ ረቂቅ ሕጉን በሚደግፉትና በሚቃወሙት የዩክሬን ፓርላማ አባላት  መካከል  በተፈጠረው አምባጓሮ እና ድብድብ አንድ የፓርላማ አባል ተጎድተው ሆስፒታል ገብተዋል።

ጠቡ የተቀሰቀሰው፣ የሩሲያን ቋንቋ መጠቀም አግባብ አይደለም የሚሉ የፓርላማ አባላት የአፈ ጉባዔውን ሥፍራ በመዝጋት ሰብሰባው እንዳይጀመር በማድረጋቸው ነው::

ከውጭ  የነበሩ ከ200 በላይ ተቃዋሚዎች በበኩላቸው  የአፈ-ጉባኤውን ስፍራ የዘጉትን የፓርላማ አባላት በመደገፍ  ተቃውሟቸውን በጩኸት

ማሰማታቸውን የጠቀሰው የዜና አውታሩ፤ የመንግሥት ደጋፊ የሆኑ የፓርላማ አባላት የተቃዋሚዎቹን ድርጊት ለማስቆም ሲንቀሳቀሱ ፓርላማው ወደ ቦክስ መድረክነት መቀየሩን አመልክቷል።

ተቃዋሚዎቹ፦በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የሩሲያ ቋንቋ መጠቀምን  የሚደግፈው ረቂቅ ሕግ የአገሪቱን ቋንቋ ይጎዳል፤ለመማርና ማስተማሩ ከፍ ያለ አገራዊ ሀብት ይባክናል ባይ ናቸው።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide