ግንቦት ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ታዋቂው የሰብአዊ መብቶች ጠበቃ የሆነው ሂውማን ራይትስ ወች ዛሬ ባወጣው ዘገባ ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ልዩ የፖሊስ ሀይል በምስራቅ የሶማሊ አካባቢ መጋቢት ወር ውስጥ 10 ሰዎችን መግደሉን ፣ የሂውማን ራይትስ ወች የእውነት አጣሪ ቡድን ወደ ሶማሊላንድ ተጉዞ ለማጣራት መቻሉን ገልጧል።
እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር መጋቢት 16 የልዩ ፖሊስ አባላት በጋሻሞ ወረዳ ራቅዳ በምትባል መንደር ውስጥ ጓደኛውን ከጥቃት ለመከላከል በሚሞክር ነዋሪ ላይ በመተኮሳቸው የአካባቢው ነዋሪዎች በብስጭት 7 የልዩ ሀይል አባላትን ገድለዋል። የልዩ ሀይሉ በወሰደው የአጸፋ እርምጃ 10 ወንዶችን በቁጥጥር ስር በማዋል ረሽነዋቸዋል፣ ከነዋሪው ጋር በተደረገው የተኩስ ልውውጥ ደግሞ 9 ነዋሪዎችን ገድለዋል፣ 24 ወንዶችን ደግሞ ይዘው ወስደዋል። የልዩ ሀይሉ የተለያዩ ቤቶችንና ሱቆችን መዝረፉን ገልጧል።
በልዩ ፖሊስ አባላት ላይ የደረሰው ጥቃት ፣ በነዋሪው ላይ የደረሰውን ጥቃት ተገቢነት አያመለክትም ሲሉ የሂውማን ራይትስ ወች የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ሌስሊ ሊፍኮው ገልጠዋል። በነዋሪው ላይ የተወሰደው እርምጃ የኢትዮጵያ መንግስት ይህን በህግ የማይገዛ ሀይል ማሰሪያ እንዲያበጅለት የሚያሳስብ ነው ሲሉ ሌስሊ አክለዋል። ባለስልጣኑዋ የኢትዮጵያ መንግስት እርምጃውን የወሰዱትን ለህግ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል።
የልዩ ሀይሉ በሶማሊ ክልል ተመሳሳይ አሰቃቂ ግድያዎችን እንደሚፈጽም ሪፖርቱ ያመለክታል። ልዩ ሀይል እየተባለ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ተጠሪነቱ ለማን እንደሆን ባይታወቅም፣ የኢትዮጵያ መንግስት የትጥቅና ምግብ አቅርቦት እንዲሁም ስልጣናና ደሞዝ እንደሰጣቸው ድርጅቱ አስታውቋል።
ሂውማን ራይትስ ወች መረጃውን ያገኘው ቃለምልልስ ከተደረገላቸው 30 የጉዳቱ ሰለባዎች፣ የተጎጂዎች ዘመዶችና የአካባቢው ነዋሪዎች ነው። መጋቢት 17 የልዩ ፖሊስ ሀይል ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ባደረጉት የተኩስ ልውውጥ 7 የፖሊስ አባላት መገደላቸውን ተከትሎ፣ ወታደሮቹ 23 ወንዶችን በመኪና ጭነው ጋልካ ወደሚባል ቀበሌ ወስደዋቸዋል። በመንገድ ላይ 5 የአካባቢውን ተወላጆች ከመኪና ላይ እንዲወርዱ በማድረግ ረሽነዋቸዋል። መጋቢት 17 ደግሞ አዳዳ በሚባል አካባቢ በሁለት መኪኖች ሲጓዙ የነበሩ የልዩ ሀይል አባላት ተኩስ በመክፈት 4 ነዋሪዎን ገድለዋል። የአካባቢው ነዋሪዎች ሟቾችን ለመቅበር ወደ ቀብር ስፍራ ሲሄዱ የልዩ ሀይሉ ፖሊስ አባላት ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር የተኩስ ልውውጥ አድርገው አምስት ነዋሪዎችን ገድለዋል። ልዩ ሀይሉ አራት ነዋሪዎች በመያዝ እረሽነዋቸዋል። አንድ ሴት የእንስሳት ሀኪም የነበረው ወንድሟን ፖሊሶቹ ከቤት አስወጥተው ግንባሩ ላይ ከተኮሱበት በሁዋላ ጉሮሮውን ቆርጠውት ሄደዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በኦጋዴን ለሚፈጸመው የስብአዊ መብቶች ጥሰት የሚሰጠው መልስ ፣ አካባቢውን ለጋዜጠኞች እና ለሰብአዊ መብት ድርጅቶች በመዝጋት ነው ሲል ደርጅቱ ኮንኗል። ድርጅቱ ለጋሽ አገራት የኢትዮጵያ መንግስት አካባቢውን ለጋዜጠኞችና ለሰብአዊ መብት ድርጅቶች ክፍት እንዲያደርግ ተጽኖ እንዲያሳርፉ ጠይቋል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide