ግንቦት ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በኢትዮጵያ የሚገኙ የጋዜጦችና የመጽሔቶች አሳታሚዎች የመንግሥትን ኢፍትሃዊ ጫና ለመቋቋም “የኢትዮጵያ ፕሬስ አሳታሚዎች ማህበር” (ኢፕአማ) የተሰኘ ማህበር ለማቋቋም በመሠረታዊ ሃሳቡ ላይ ትናንት ከሥምምነት ላይ መድረሳቸውን ምንጮች አስታወቁ፡፡
ትናንት ረቡዕ ግንቦት 15 ቀን 2004 ዓ.ም በአቶ አማረ አረጋዊ “ሆርን ኦፍ አፍሪካ ፕረስ ኢንስቲቲዩት” ቢሮ የተሰባሰቡት አሳታሚዎች በቅርቡ በብርሃንና ሰላም እና ቦሌ ማተሚያ ቤት የወጣውን አስገዳጅ መንግሥታዊ ውል ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ ሰዋዊና ሕገመንግሥታዊ መብት ይጥሳል ሲሉ የተቃወሙ ሲሆን ፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ አሳታሚዎች ማህበር በሚቀጥለው ረቡዕ በሚጸድቀው መተዳደሪያ ደንቡ ላይ እንደተገለጸው ቢሮ በዋናነት በአዲስ አበባ ሆኖ እንደ አስፈላጊነቱ በክልሎችም ሊከፍት ይችላል፡፡
በዓላማውም ለትርፍ ያልተቋቋመ ሆኖ የአሳታሚዎችን መብት ማስጠበቅ፣ ጠንካራ ፕሬስ እንዲኖር ማድረግ፣ በፕሬስ ዙሪያ የሚወጡ ፖሊሲዎች ላይ ተጽዕኖ እንዳይፈጠር ዘብ መቆም ይሆናል፡፡
አሳታሚዎቹ ከመንግስት የእጅ አዙር ጫና በዘላቂነት ለመላቀቅም የራሳቸው የሆነ ማተሚያ ቤት ለማቋቋም በመሠረታዊ ሃሳቡ ከሥምምነት ላይ የደረሱ ሲሆን “የኢትዮጵያ ሚዲያ ዴቨሎፕመንት ፈንድ የአክሲዮን ማህበር” ለማቋቋም የመመሥረቻ ጽሑፍና የመተዳደሪያ ደንብ አርቅቀው እየተወያዩበት ሲሆን በሚቀጥለው ረቡዕ ያጸድቁታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
“የኢትዮጵያ ሚዲያ ዴቨሎፕመንት ፈንድ የአክሲዮን ማህበር” በአሳታሚዎችና አክሲዮን በሚገዙ ባለሃብቶች በብር 500፡000 (አምስት መቶ ሺህ) ካፒታል የሚመሠረት ሲሆን የራሱ የሆነ ማተሚያ ቤት በማቋቋም የሕትመት ሥራዎችን ማከናወን፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂን በህትመት ኢንዳስትሪው ውስጥ ማስተዋወቅ፣ ሚዲያ ነክ በሆኑ ሌሎች ኩባንያዎች ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ዋና ዓላማው ይሆናል ተብሏል፡፡
ባለፈው ዓርብ ረፋዱ ላይ ከብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ጋር ለውይይት የቀረቡት የጋዜጦችና መጽሐየቶች አሳታሚዎች ማንኛውም ውል በተዋዋይ ወገኖች በጋራ የሚጸድቅ መሆኑን አውስተው ፣ ብርሃንና ሰላም በህግ የሚያስጠይቅ ነገር ያለው ከመሰለኝ አላትምም በሚለው አዲስ አስገዳጅ ውል ላይ እነርሱም ማተሚያ ቤቱ ለሚፈጥረው ህትመት መበላሸት፣ መዘግየትና ቀጠሮ አለማክበር ካሳ እንዲከፍል የሚሉ ነጥቦች እንዲካተትላቸው በጽሑፍ በማቅረባቸው ማተሚያ ቤቱ ሁኔታውን ለማገናዘብ ጊዜ ያስፈልገኛል ብሎ በአንድ ሳምንት ውስጥ ለውይይት እጠራችኋለው ብሎ ማሰናበቱ ይታወሳል::
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide