ግንቦት ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የቀድሞው የአፍሪካ ጉዳዮች ሊቀመንበርና አሁን ሽብርተኝነትን፣ አውዳሚ የጦር መሳሪያን እና ንግድን የሚመለከቱ ጉዳዮችን የሚመለከተውን ኮሚቴ የሚመሩት ኤድዋርድ ሮይሲ ለአቶ መለስ ዜናዊ በጻፉት ደብዳቤ ፣ በእስር ላይ ስለሚገኙት ጋዜጠኞችና የፖለቲካ እስረኞች እንዲሁም በአገሪቱ ውስጥ ስላለው የፕሬስ አፈና ያላቸውን ስጋት ገልጠዋል።
ያለ ፕሬስ ጠንካራ የሆነ ዲሞክራሲያዊ ስርአት መገንባት እንደማይቻል የገለጡት ሮይስ፣ በአገር ደህንነትና ሽብርተኝነትን በመዋጋት ስም የፕሬስ መብቶች እየታፈኑ ጋዜጠኞችም እየተዋከቡ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች ለፍርድ ቢቀርቡም ፣ የፍርድ ሂደቱ አለማቀፍ መስፈርቶችን ያሟላ አለመሆኑ እና በእስረኞች ላይ በቴሌቪዥን ፕሮፓጋንዳ መሰራቱ ጉዳዩ ፖለቲካዊ መሆኑን ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ ጠቃሚ የሆነ የኢኮኖሚ እድገት ብታስመዘግብም ፣ በፕሬሱ ላይ የሚታየው አፈናና የፍርድ ቤት ነጻነት አለመኖር እነዚህን አወንታዊ ለውጦች እንደሸፈናቸው ባለስልጣኑ ተናግረዋል።
ሴናተር ማርክ ቤጊች በበኩላቸው የኦባማ አስተዳዳር በደህንነትና በኢኮኖሚ ሰበብ ከአምባገነን መንግስታት ጋር መወደጃቱ ለአሜሪካ ዘላቂ ጥቅም ጎጂ መሆኑን ከሰሜን አፍሪካ ቅርብ ተመክሮ መረዳት ይቻላል ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን የአቶ መለስን በቡድን 8 አገራት ስብሰባ ላይ መጋበዝ በተመለከተ ያሳዩት ተቃውሞ ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚፈጸመው የሰብአዊ መብት ጥሰት የአሜሪካ ፖለቲከኞች ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት መጀመራቸውን ያሳያል የሚሉ አስተያየቶች ቀርበዋል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide