በሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በስጋት ላይ ናቸው

ግንቦት ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ሱዳን የሚገኙ የኢትዮጵያ ስደተኞች የደህንነት ዋስትናቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ አደጋ ውስጥ እየወደቀ መምጣቱን ተናገሩ። ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ስደተኞች ለኢሳት እንደገለጡት ፣ የኢትዮጵያ መንግስት በወንጀለኝነት የሚጠረጥራቸውን በሱዳን ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን፣ የአገሪቱ መንግስት አሳልፎ እንዲሰጠው የሚያስችል ስምምነት ማድረጉ፣ በህልውናቸው ላይ ተጨማሪ ስጋት ፈጥሯል።

የሱዳን መንግስት የመለስን መንግስት ተቃውመው ወደ አገሩ የሚገቡ ኢትዮጵያውያንን እያሳለፈ እንደሚሰጥ ቢታወቁም፣ በሁለቱ መንግስታት መካከል ትናንት የተፈረው ወንጀለኞችን የመለዋወጥ አዲስ ስምምነት፣ የበርካታ ኢትዮጵያውያንን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ነው። በስምምነቱ መሰረት ወንጀለኛ የሚባሉት የመለስን መንግስት የሚቃወሙ ሁሉ ናቸው የሚሉት አንድ ለስምምነቱ ቅርበት ያላቸው ዲፕሎማት፣ የሱዳን መንግስት አለማቀፍ ህግጋትን በሚጥስ መልኩ እንዲህ አይነት ስምምነት መፈራረሙ፣ የመለስ መንግስት የኢትዮጵያን መሬት ለሱዳን ቆርሶ መስጠቱ የአገሪቱን መንግስት በማስደሰቱ የመጣ ሊሆን እንደሚችል ገልጠዋል። የመለስን መንግስት የሚቃወሙ እና በሱዳን ጥገኝነት የጠየቁ በርካታ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን ያወሱት ዲፕሎማቱ፣ ስምምነቱ ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥ የሚደርስባቸውን ጭቆና ሸሽተው ወደ ሱዳን እንዳይገቡ የሚያደርግ ነው ሲሉ አክለዋል።

በሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንደሚሉት ወትሮም ቢሆን በቂ ከለላ የማይሰጣቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን፣ አዲሱን ስምምነት ባለመቃወሙ ማዘናቸውን ገልጠዋል። የሱዳን መንግስት በሽብረተኝነት ወንጀል የተከሰሰውንና በእስር ላይ የሚገኘውን አቶ አንዱአለም አያሌውን ለኢትዮጵያ መንግስት አሳልፎ መስጠቱ ይታወቃል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide