ግንቦት ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ድረ-ገጹ የስብሰባ ምንጮቹን በመጥቀስ እንደዘገበው፤ችግሩ የተጀመረው ገና ጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴው ዝርዝር የመወያያ አጀንዳዎቹን ለምልአተ ጉባኤው ሲያቀርብ ነው።
ኮሚቴው ካቀረባቸው 20 አጀንዳዎች ውስጥ ርእሰ-መንበሩ አቡነ ጳውሎስ በተራ ቁጥር 18 ላይ በሰሜን አሜሪካ በስደት ከሚገኙ አባቶች ጋራ የተጀመረው ዕርቅ ጉዳይ በአጀንዳነት መያዙን ይቃወማሉ።
የ እርቁ ጉዳይ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላትም፦ “ፖሊቲከኞች ናቸው” በሚልም በዕርቀ- ሰላሙ ሂደት መቀጠል ላይ እንደማያምኑበት ይናገራሉ።
አቡነ ጳውሎስ በዚህ ሳያቆሙም ከመንበረፓትርያርኩ ተወክለው ከሄዱት ልኡካን መካከል አንዱን አባል በስም በመጥቀስ ፦“ወደኋላ ቀርተው ከእነርሱ ጋራ ነገር ሲሸርቡብኝ ነበር” በማለት ወቀሳ ይሰነዝራሉ፡፡
ይሁንና አቡነ ጳውሎስ በሰሜን አሜሪካው የዕርቅ አጀንዳ ላይ ስለሰነዘሩት ተቃውሞ ሐሳባቸውን የሰጡ በርካታ አባቶች÷ “በእኛ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ለሁለት ተከፍላ አትቀርም! ለቀጣዩ ትውልድ ለሁለት የተከፈለች ቤተ ክርስቲያን ማስረከብ አንሻም፤ የዕርቅ ሂደቱ መቀጠሉ ግድ ነው፤ በእግራችንም ቢኾን እዚያው ሄደን እናሳካዋለን”በማለት ከፓትርያርኩ ጋር ጠንካራ ምልልሶችን ጋራ ተለዋውጠዋል፡፡
በአንጻሩፓትርያርኩ በዕርግና እና በሞተ ዕረፍት የተለዩ አባቶችን በመቁጠር ተጨማሪ ኤጲስ ቆጶሳት መሾም እንዳለባቸው ከምልዓተ-ጉባኤው ተለይተው ከዚህ ቀደም የያዙትን አቋም በ ሲኖዶሱ ስብሰባ በድጋሚ አንጸባርቀዋል።
ሲኖዶሱ ግን ይህንም ሃሳባቸውን አልተቀበላቸውም።
አቡነ ጳውሎስ ያለማሳለስ እየተሟገቱበት ያለውንና በብዙዎች ዘንድ “የፓትርያርኩ አዳዲስ የዓላማና ጥቅም ወዳጆች ማፍሪያ ነው” የሚባለውን የተጨማሪ ኤጴስ ቆጶሳት ሹመት ጉዳይ፦ “ለጊዜው ያለነው እንበቃለን፤ ከተጀመረው ዕርቅ አንጻር ወቅቱን የጠበቀ አይደለም፤ የዕርቁን ሂደት ያደናቅፋል፤ ያለውንም ችግር ያባብሳል” በሚል ነው ብዙሀኑ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ሀሳቡን ውድቅ ያረጉት፡፡
በመካከል የወዲያውንም የወዲሁንም ሐሳብ በመዳኘት ለመሸምገል የሞከሩ ብፁዓን አባቶች የነበሩ ቢኾንም ፤ምልአተ ጉባኤው መግባባት ላይ ሳይደርስ ለምሳ ለእረፍት ተበትኗል።
ከቀትር በኋላ ቅዱስ ሲኖዶሱ ወደ አጀንዳው በመግባት መወያየቱን እንደሚቀጥል ብዙዎቹ ተስፋ ቢያደርጉም፤አቡነ ጳውሎስ በፈፀሙት ተግባር የሲኖዶሱ ስብሰባ እስመቋረጥ ደርሷል።
ለስብሰባው ምክንያት ዋነኛው ምክንያት ብፁአን ሊቃነ-ጳጳሳቱ ከምሳ መልስ ወደ አዳራሹ ሲገቡ በየጠረጴዛቸው ላይ “ዜና-ቤተ-ክርስቲያን”የተሰኘውን ጋዜጣ ያገኛሉ።
ጋዜጣውን ከርዕሱ ጀምሮ ወደ ውስጥ ሲመለከቱትም የአቡነ-ጳውሎስን ሀሳቦች ከማንጸባረቅ አልፎ ብዙሀኑን በተለይም የአቡነ-ጳውሎስን ሀሳብ እና አቅጣጫ የሚቃወሙትን ጳጳሳት በሚያሸማቅቁ ጽሁፎች የተሞላ ሆነው ያገኙታል።
በዚህን ጊዜ የቅዱስ ሲኒዶሱ አባላት ጋዜጣው ከይዘቱ በተጨማሪ በስብሰባ መካከል እንዲሰራጭ መደረጉ ብጹአን አባቶችን ለማሸማቀቅ እንደሆነ ተናግረዋል።
እንደ ደጄ ሰላም ዘገባ፤የጋዜጣው ርእሰ አንቀጽና ዘገባዎች አባጳውሎስ በስብሰባው እንዲያዙላቸው የሚፈልጓቸውን አጀንዳዎች ከአባጳውሎስ “የፓትርያርክነት ዐምባገነንነት” ፍላጎት አንጻር የማብራራት ግብዝነት የሚታይበት ነው።ይህንን ተከትሎ አባጳውሎስን ከፓትርያርክነት ማዕርጋቸው ሊያወርዷቸው በሚችሉ የቃለ መሐላ ጥሰትና የታማኝነት መታጣት ጉዳዮች ዙሪያ ጠንካራ ውይይት ተጀመረ።
ይሁንና ይህ ውይይት መጀመሩ ያስቆጣቸው የአባጳውሎስ ግብረ በላዎች ከትናንት በስቲያ ምሽት እና ትናንት ቀን ላይ በአባቶች ማረፊያ ቤት እየተዘዋወሩ በማስፈራራት፤ የ አባቶችን ጽናትና አንድነት ለማላላት ሞከሩ።
በዚህ ተግባር ውስጥ እጅጋየሁ በየነ፣ ኀይለ ጊዮርጊስ ጥላሁንና ለጊዜው ስማቸው ያልተጠቀሱ ግለሰቦች እንደሚገኙበት ድረ–ገጹ አመልክቷል።
ባለፈው ዓመት በተካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ የአቡነ–ጳውሎስን ሀሳብ የተቃወሙ ሊቃነ–ጳጳሳት በሌሊት የማረፊያ ቤታቸው በር ተሰብሮ የድብደባ ሙከራ እንደተደረገባቸው መዘገቡ ይታወሳል።
አለመግባባቶቹ እየተካረሩ እና ወደ መጥፎ አዝማሚያ እያመሩ መሆናቸውን ያስተዋሉ አንድ አባትም በቀጥታ አቡነ–ጳውሎስን፦“ከእርስዎ ጋራ መነጋገር አልቻልንም፤ ወደ አጀንዳ ሳንገባ በየቀኑ ከእርስዎ ጋራ ንትርክ ሰልችቶናል፤ ሦስተኛ አካል ይግባ፤ መንግሥት ይግባና ይዳኘን ” እስከማለት ይደርሳሉ፡፡
ይኹንና የስብሰባው ምንጮች እንዳሉት፤ይህ ሐሳብ ወዲያው ነበር ተቃውሞ የገጠመው፡፡
“አሁን ጎራ ለይቷል፤ በአንድ በኩል ቅዱስነትዎ ብቻዎን፤በሌላ በኩል የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በሙሉ። ይህ የሚያሳየው እርስዎ ፤ ለአብዛኛው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ድምጽ ተገዥ አለመሆንዎን ነው፤” በማለት አቡነ-ጳውሎስን የነቀፉ አንድ ሌላ ብፁዕ አባት፤ “ሦስተኛ ወገን የሚባል አካል አይገባም፤ አያስፈልገንም። ቅዱስ ሲኖዶስ ሕግ አውጭ፣ ሕግ ተርጓሚ፣ ሕግ አስፈጻሚ ነው፤ ስለዚህ አጀንዳዎቹን አጽድቆ መወያየቱን መቀጠል ይኖርበታል፤” በማለት አንገብጋቢ የኾኑ አጀንዳዎችን በመለየት ዘርዝረዋል፡፡
ሀሳባቸውም በብዙሀኑ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል።
በእኚህ አባት ሐሳብ መሠረት ቅዱስ ሲኖዶሱ ይህን ማድረግ ካልቻለ ፤፦ “ሁሉም ሊቃነ ጳጳሳት ስብሰባውን አቋርጠው ወደየ አህጉረ ስብከታቸው በመመለስ ለየምዕመኖቻቸው የ አቡነ–ጳውሎስን እንቢታ እንደሚያስረዱ አቋማቸውን በግልጽ ያሳውቃሉ።፤”
ሌላ ሊቀ-ጳጳስ በዚሁ ላይ አክለው፦ “ስብሰባውን ማቋረጥ ብቻ ሳይኾን ይህ ምልአተ– ጉባኤ የሚለያየው ስለ ኹኔታው ለሚዲያ መግለጫ በመስጠት ጭምር ነው” ማለታቸው ተዘግቧል
የስብሰባው ምንጮች እንዳሉት ፓትርያርኩ፦መንግሥት አካል ጣልቃ ገብቶ ያነጋግረን”በማለት አቡነ ፋኑኤል የሰነዘሩትን ሐሳብ እንደሚቀበሉት ቢግልጹም፤ “ከዚህ በፊት ተደብድበን ምን የመጣ ነገር አለ፤ በሃይማኖት፣ በአስተዳደር ጉዳይ ሲኖዶሱ የመወሰን ሙሉ ሥልጣን አለው፤” በሚል የብዙሀኑ ተቃውሞ ሐሳቡ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡
በመጨረሻም ከፓትርያርኩ በቀር የምልአተ- ጉባኤው አባላት “ስብሰባውን አናቋርጥም፤ ወደየ ሀገረ ስብከታችንም አንሄድም፤ ሌላ ሰብሳቢ መርጠን ውይይታችንን እንቀጥላለን” በሚል ውሳኔ ተበትነዋል።
በዚህም መሰረት የሲኖዶሱ ስብሰባ በዛሬው ዕለትም ቀጥሎ ውሏል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide