ሚያዚያ ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-አንድነት ለዲሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲ ባለፈው ቅዳሜ በወላይታ ሶዶ የተሳካ ስብሰባ ከካሄደ በሁዋላ በማግስቱ ደግሞ በአርባ ምንጭ በርካታ ህዝብ በተገኘበት የተሳካ ስብሰባ አካሂዷል። የከተማው መስተዳደር ለፓርቲው ስብሰባ ማካሄጃ ሲቀላ በሚባለው አካባቢ በሚገኝ የፖሊስ አዳራሽ ቢፈቅድም፣ አዳራሹ ለተሰብሳቢው በማይመች መልኩ ማዘጋጀቱን ለማወቅ ተችሎአል። በስብሰባው ላይ በርካታ ህዝብ እንደሚገኝ እየታወቀ ሲመጣ፣ የወረዳው ባለስልጣናት ነዋሪው ወደ ስብሰባው እንዳይሄድ የቡና ዝግጅት የሚሉ መርሀግብሮችንና የተለያዩ ያልተሳኩ መኩራዎችን አድርጓል። ህዝቡ በቃን እያለ በተናገረበት ስብሰባ ላይ ነጋዴው፣ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችና የመንግስት ሰራተኞች በብዛት ተገኝተዋል። የስብሰባው አዳራሽ 1 ሺ 800 ሰዎችን የሚይዝ ቢሆንም ፣ በእለቱ የተገኘው ህዝብ ብዛት ከአዳራሹ አቅም በላይ በመሆኑ ውጭ ላይ ለማዳመጥ መገደዱን ዘጋቢያችን ገልጧል።
ህዝቡ በስርአቱ በእጅጉ መማረሩን እና ለውጥ እንደራቀበት ይናገር እንደነበር የጠቀሰው ዘጋቢያችን፣ ፓርቲዎቹ ጠንክረው የሚንቀሳቀሱ ከሆነ ህዝቡ ዛሬም ከጎናቸው እንደሚቆም አክለዋል።
በአርባ ምንጭ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ስሜት መነቃቃት መፈጠሩን ፣ የአንድነት ፓርቲ አመራሮችም በህዝቡ ስሜት መደሰታቸውን ለማወቅ ተችሎአል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide