ሚያዚያ ፳፬ (ሃያ አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-እንደ ጋዜጣው ዘገባ፤በደቡብ ክልል በጉራ ፈርዳ ወረዳ ይኖሩ የነበሩ አማሮች ፦”ወደ አገራችሁ ሂዱ” ተብለው መባረራቸው ህዝባዊ ተቃውሞ ባስነሳበት
በሁኑ ጊዜ፤ በቤንሻንጉክ ጉሙዝ ክልል ይኖሩ የነበሩ የ አማራ ተወላጆችም ተመሣሳይ ዕጣ ገጥሟቸዋል።
እንዲሁም በሰሜን ጎንደር ዞን ሱዳን ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው አርማጭሆ ወረዳ ውስጥ በኢብርሀጂራ አካባቢ በእርሻ ሥራ ተሰማርተው ይኖሩ የነበሩ የአማራ ተወላጅ አርሶ አደሮች የ እርሻ መሬታቸውን ተነጥቀው ሰሞኑን መባረራቸውን፤ የአካባቢውን አርሶአደሮች ተናግረዋል።
በድርጊቱ የተበሳጩት አርሶ አደሮች፦ ኢህአዴግ በአማራ ላይ ጣቱን ቀስሯል”ሲሉ በምሬት መናገራቸውን ፍኖት ገልጿል።
ከተለያዩ ቦታዎች ከይዞታቸው እየተፈናቀሉ ያሉት አርሶአደሮች ምንም መቋቋሚያ ስላልተሰጣቸው የከፋ ችግር ላይ እየወደቁ መሆናቸውም ተመልክቷል።
ከ አርማጭሆ አካባቢ ሰሞኑን የተፈናቀሉት አርሶ አደሮች፤ ከ1998 ዓመተ ምህረት ጀምሮ በስፍራው ሲኖሩ የቆዩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አርሶ አደሮች ከይዞታቸው በሚነሱበት ጊዜ፦”መሬቱ በብሎክ ስለሚደለደል፤ ያለሰለስኩት ማሳዬ ስለሆነ ለኔ ይገባኛል “የሚል ጥያቄ እንዳያነሱ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸውም ገልጸዋል።
አርሶ አደሮቹ የተፈናቀሉት መንግስት አካባቢውን ቆርሶ ለሱዳን በመሰጠት በመወሰኑ እንደሆነ ተገልጿል።
ከዚህም ባሻገር፤በታች አርማጭሆ ወረዳ ፤ሳንጃ ውስጥ ለረጂም ዓመታት የቤተ-ክርስቲያን መገልገያ የሆነን ሥፍራ “ለልማት” ተብሎለአንድ ባለሀብት እንዲሰጥ በመወሰኑ ፤በአካባቢው ህብረተሰብ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ መፈጠሩን ጋዜጣው ጨምሮ ዘግቧል ፡፡
የአካባቢው ህብረተሰብ በውሳኔው መቆጣቱ ያሣሰባቸው የወረዳው ኃላፊዎች ህዝቡን ሰብስበው ለማግባባት ቢሞክሩም ህዝቡ በተቃውሞው በማምረሩ በአካባቢው ውጥረት መንገሱን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
ወረዳው፤ በምርጫ 97 ኢህአዴግ አንድም ድምጽ ያላገኘበት አካባቢ በመሆኑ ፤ ነዋሪው በተለይ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ባሉት ዓመታት ከፍ ያለ አስተዳደራዊ በደል ሲፈጸምበት መቆየቱን የዜናው ምንጮች አስታውሰዋል።
“በአሁኑ ጊዜ የአካባቢውን ህብረተሰብ ነፃነቱ ሙሉ በሙሉ ተገፏል፤ሁሉም ዜጋ የቁም እስረኛ ተደርጓል፡፡ ከሚኖርበት
ቀበሌ ወደ ሌላ ማናቸውም ቀበሌ ለመሄድ ቢፈልግ እንኳ፤ ለአካባቢው ኃላፊዎች አሳውቆ የይለፍ ወረቀት መያዝ ይጠበቅበታል፡፡
የፍቃድ ወረቀት ሳይኖረው ከሚኖርበት ቀበሌ ተነስቶ ወደ ሌላ ቀበሌ ቢሄድ ይታሰራል” ሲሉም- በ አካባቢው የሚታየው ውጥረት ምን ያህል የከፋ እንደሆነ ምንጮቹ ለማመልከት ሞክረዋል።
መንግስት በዋልድባ የስኳር ፋብሪካ ለመስራት የጀመረውን እንቅስቃሴ ተከትሎ ውጥረት ነግሶ መቆየቱ የሚታወቅ ሲሆን፤ ከሰሞኑ ደግሞ የሰሜን ጎንደር ህዝብ ዶማ፣ አካፋና ጦር እየያዘ ወደ ስፋራው እየተመመ እንደሚገኝ መዘገቡ ይታወሳል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide