የተመድ ሰራተኞች መታሰር የድርጅቱን ድክመት ያሳያል ተባለ

ሚያዚያ ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም  

ኢሳት ዜና:-የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰራተኞች ያለ አግባብ በኢትዮጵያ ዉስጥ መታሰር የድርጅቱን ድክመት ያሳያል ሲል ክርስቲያን ሳይንስ ሞኒተር የመረጃ ምንጭ ገለፀ

የኢትዮጵያ መንግስት ከአንድ አመት በላይ ክስ ሳይመሰረትበት አንድ የድርጅቱን ሰራተኛ እስር ቤት እንደጣለዉና አንድ ሌላ ሰራተኛ ደግሞ በፀረ ሽብር ህግ ተከሶ በእስር ላይ መገኘቱን በማመልከት በአፍሪቃ ቀንድ በምእራባዊያን የሚደገፈዉ አናሳ የመለስ ዜናዊ ህገ ወጥ ቡድን የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን አጣብቂኝ ዉስጥ እንደጣለዉ መረጃዉ አብራርቷል።

በኢትዮጵያ /የኤች አይ ቪ ኤድስ/ መድሃኒት ስርጭትን ጨምሮ በበርካታ የጤና እና በሌሎች የርዳታ ተግባሮች ከመንግስት ጋር ተባብረዉ የሚሰሩ 27 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት  መኖራቸዉን የጠቀሰዉ መረጃ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስራ ሃላፊዎች በአካባቢዉ በመደጋገም በስራ ጉዳይ ቢገኙም ኢትዮጵያዊ ዜግነት ባለዉ የአካባቢ የፀጥታ ረዳት ሰራተኛ የሆነዉ ዩሱፍ መሃመድ ከታህሳስ 2010 ጀምሮ በክልል እስር ቤት ዉስጥ ክስ ሳይመሰረትበት በመሰቃየት ላይ ስለመሆኑ ጥያቄ አልቀረበም።

የኢትዮጵያ መንግሰት ግለሰቡን ያሰረዉ በአገር ዉስጥ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችን በገንዘብ ይደግፋል በመባል የሚጠረጠር ነዋሪነቱ በዴንማርክ የሆነ ወንድሙ ተላልፎ እንዲሰጠዉ ለማድረግ ባለዉ ሃሳብ እንደሆነ የሰብኣዊ መብት ተሟጋቾች ይናገራሉ።

የዩሱፍ መሃመድ የስራ ባልደረባና የመንግስታቱ ድርጅት የደህንነትና የፀጥታ ክፍል ሰራተኛ የሆነዉ አብዱረህማን ሼክ ሃሰን ተጠልፈዉ የነበሩ ሁለት የአለም ምግብ ፕሮግራም ሰራተኞችን ከኦጋዴን ብሄራዊ ነፃ አዉጪ ግንባር /ኦብነግ/ጋር በመደራደር ካስለቀቀ በሁዋላ ከድርጅቱ ጋር ግንኙነት እንዳለዉ ተወንጅሎ በፀረ ሽብር ክስ ተመስርቶበት በእስር ላይ እንደሚገኝ ታዉቋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በአለም አቀፍ ርዳታ የሚንቀሳቀስ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን የሚከተለዉን ፖሊሲ የሚቃወሙትን የመንግስታቱን ድርጅትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሰራተኞችን ከአገር እንዲባረሩ በማድረግ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያላቸዉን ደግሞ እንደሚያስር፤ በጉምሩክ አማካይነት ወዳገር የሚገቡ የመንግስታቱን ድርጅት እቃዎችን እንደሚወርስ፤ለድርጅቱ ሰራተኞች የትዳር ጓደኞች የስራ ፈቃድ እንደሚነፍግ፤  53 አመታት ያስቆጠረዉን  አገሪቱ የፈረመችዉን አለም አቀፍ ዉል በመፃረር የመንግስታት ድርጅቱን ተሽከርካሪዎች እንደሚፈትሽ ታዉቋል።

ይኸዉ የኢትዮጵያ  መንግስት አለም አቀፍ ህግን በመፃረር የሚፈፅማቸዉ ተግባራት በዲፕሎማቲክ ደረጃ በተሰየሙ ሰዎች ላይ ሳይቀር የሚንፀባረቅ ለመሆኑ ባለፈዉ ጥቅምት ወር በኢትዮጵያ የስሎቫኪያ አምባሳደር የሆኑትን ሚላን ዱብቼክ በፀጥታ ሃይሎች ከመንገድ ተይዘዉ መታሰራቸዉን በምሳሌነት በመጥቀስ አመልክቷል።

“ባለፈዉ አመት ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦች በህገወጥ መንገድ መታሰራቸዉን አምናለሁ፤ ይህ እየተስፋፋ የሄደ የተለመደ አሰራር ነዉ፤ በኢትዮጵያ የሚገኙ እስር ቤቶችን በገለልተኛ አካል መቆጣጠር ባለመቻሉ ትክክለኛዉ የእስረኛ ቁጥር ማወቅ እንደማይቻል ሂዩማን ራይትስ ዎች እና አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሚያዉቁት ነዉ “ በማለት የሂዩማን ራየትስ ዎች ባለስልጣን ላኤቲ-ትያ ባርደር  መግለፃቸዉን ክርስቲያን ሳይንስ ሞኒተር ጠቅሷል።

የመለስ መንግሰት በ2009 ባወጣዉ ህግ መሰረት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ለማፈን እንደቻለዉ ሁሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ለማፈን ፍላጎት እንዳለዉ በመረጃዉ ተገልጿል።

ይሁን እንጂ 5 የመንግስታቱ ድርጅት ልዩ የመብት ራፖርተሮች የኢትዮጵያ መንግስት በዜጎች ላይ የሚያደርሰዉን የመብት ረገጣ ባለፈዉ የካቲት ወር ባወጡት መግለጫ ማጋለጣቸዉን፤ አምና የአለም የገንዘብ ድርጅት /አይ ኤም ኤፍ/ የኢትዮጵያ መንግስት ማእከላዊ ባንክ የሚከተለዉ የተዛባ የብድር ፖሊሲ አስከፊ የእቃዎች ዋጋ ግሽበት እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑን፤ እንዲሁም የመንግስታቱ ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ የግቤ 3 የአሌሌክትሪክ ሃይል ግድብ ግንባታን በተመለከተ መንግስት በመዉሰድ ላይ ያለዉን እርምጃ አጥብቆ መንቀፉን ክርስቲያን ሳይንስ ሞኒተር ጋዜጣ አመልክቷል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide