የፌዴራል አቃቤ ህግ በፍትህ ጋዜጣ ላይ አቤቱታ አቀረበ

መጋቢት ፳፯ (ሃይ ሰባት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- “ፍትህ ጋዜጣ የተከሳሾችን ቃል ብቻ በጋዜጣ በማስተናገድና ዐቃቤ ሕግ ከመንግሥት ፖለቲካዊ ጫና ነፃ ሆኖ እንደማይሰራ በማተት በህዝብ ላይ እምነት እንድናጣ አድርጎናል ሲል”የፌዴራል አቃቤ ህግ አቤቱታ አቀረበ።

 አቃቤ ህግ ይህን ክስ ያቀረበው፤ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ትናንት ከሰዓት በኋላ በእነአንዷለም አራጌ የክስ መዝገብ በማረሚያ ቤት ሆነው ከሚከራከሩ ስምንት ተከሳሾች ውስጥ የ5ተኛ ተከሳሽ ክንፈሚካኤል ደበበንን ሦስት የመከላከያ ምስክሮች ባደመጠበት ወቅት ነው፡፡

ፍርድ ቤቱም፤ የአቤቱታ ክሱ በጽሑፍ እንዲቀርብለት እንዲሁም የጋዜጣው  ዋና አዘጋጅ በመጥሪያ ተጠርቶ ፍርድ ቤት እንዲቀርብና ሁኔታውን እንዲያስረዳ ብይን አስተላልፏል፡፡

በዛሬው የከሰዓት በኋላ የችሎት ውሎ የክንፈሚካኤል ደበበ  የመከላከያ ምስክር ሆነው የቀረቡት ፤ የቀድሞው ብርሃን ለአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበርና አሁን የአንድነት ፓርቲ አመራር አባል የሆኑት አቶ ሙላቱ ጣሰው፣  የመድረክ  የአመራር አባል የሆኑት የኦፌዴኑ አቶ ኡርጌሳ ዋኬኔ እና ጋዜጠኛ ብዙአየሁ ወንድሙ  ናቸው።

ምስክሮቹ ፤ተከሳሹ በሠላማዊና ህጋዊ መንገድ መንግስትን እንደሚቃወም ፣ በመስከረም ወር 2004 ዓ.ም  ሠላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫና በራሪ ወረቀት ማዘጋጀቱንና የሰልፍ ፈቃድ መጠየቁን እንደሚያውቁና ይሄም የመንግስቶቹን ጨምሮ በሌሎችም ብዙሃን መገናኛዎች  መዘገቡን አስረድተዋል።

በአንድነት ፓርቲ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ በመገኘትም፤ ስለ ሰላማዊ ትግል ሃሳብ ማካፈሉን መስክረዋል፡፡

የ6ተኛ ተከሳሽ አቶ ምትኩ ዳምጤ ተጨማሪ የመከላከያ ምስክር ሆነው ከማረሚያ ቤት የመጡት አቶ ኢፋ ጉዲና በበኩላቸው፤ በወቅቱ ከአቶ ምትኩ ጋር ማዕከላዊ እስር ቤት አብረው አንድ ክፍል መታሰራቸውንና አቶ ምትኩ በፖሊሶች ተጠርተው ቶርች ተደርገውና ተደብድበው ሲመለሱ እና በግድ ቃል ስጡ ተብለው ሲፈርሙ መመልከታቸውን መስክረዋል፡፡

የተከሳሾቹ ምስክሮች ከተደመጡ በሁዋላ ነበር አቃቤ ህግ በጋዜጦች ላይ የክስ አቤቱታ ማሰማት የጀመረው።

 “ለፍርድ ቤቱ ማመልከቻ አለኝ” በማለት ፈቃድ የጠየቀው የፌዴራል ዐቃቤ ህግ፤ በተለይ ፍትህና ነጋድራስ ጋዜጦች በህብረተሰቡ ዘንድ ያለውን ተዓማኒነት እየሸረሸሩበት መሆኑን  ተናግሯል።

“ተከሳሾች በአንቀጽ 142/3 መሠረት የተከሳሽ ቃላቸውን መስጠት ከጀመሩ ጀምሮ የችሎት ዘገባ የሚያቀርቡ ጋዜጦች በተለይ ፍትህ ጋዜጣ እንዲሁም ነጋድራስ ጋዜጣ ችሎቱን በመዳፈር የፍትህ ሥርዓቱን በሚያናጋና እምነት ሊጣልበት እንዳይችል በማድረግ አንባቢያን በዐቃቤ- ሕግ ሥራ ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርባቸው” እያደረጉ ነው  ብሏል-ፌዴራል ዐቃቤ ህግ።

“ጋዜጦቹ ፤አቃብያነ  ህጎች በመንግሥት ፖለቲካዊ ጫና እንደሚደረግብንና በሀሰት ክስ እንደምናቀርብ በማስመሰል፣ ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን ሳይመረምር ብይን እና ፍርድ እንደሚሰጥ ትርጉም የሚሰጥ ዘገባ እያቀረቡ ነው” ያለው ዐቃቤ ህግ፤ “ከዚህም በላይ  ለፍርድ ቤቱ ከመንግሥት  ውሳኔ ተጽፎ እንደሚሰጠው የሚመስል ዘገባ እያቀረቡ” ነው ብሏል፡፡

አቃቤ ህግ አቤቱታውን በመቀጠል፦”ይህም ፍርድ ቤቱ በህዝብ ላይ ያለውን አመኔታ የሚያሳጣ ነው።እንዲሁም ተከሳሾቹ በንግግር ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡትን ቃል ለኢትዮጵያ ህዝብ እንደተደረገ ንግግር እያደረጉ የችሎት አዘጋገብ ደንብን ባልተከተለ መልኩ ቀድመው ፍርድ እየሰጡ ነው”ሲልም አማሯል።

አቃቤ ህግ  ለዚህ ማሳያ ይሆኑልኛል  ያላቸውን  የፍትህ ጋዜጣ እትሞችን ለችሎቱ  በዋቢነት አቅርቧል፡፡

“ከዚህም በላይ በችሎቱ ያላቀረብናቸው ብዙ ነገሮች እየተባሉ ነው” ያለው ዐቃቤ ህግ፤  “ፍርድ ቤቱ ይሄን ተገንዝቦ ተከሳሾቹ በሰጡት ቃል ላይ ፍርድ ቤቱ ብይን እንዲሰጥበት እና ጋዜጦቹ ላይ ብይን ተሰጥቶ የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ እንጠይቃለን” ሲል አቤቱታውን አሰምቷል።

አቃቤ ህግ ሮሮውን በመቀጠል፦”በተለይ የፍትህ ጋዜጣ  አዘጋጅ ቀርበው ሁኔታውን እንዲያስረዱ እንጠይቃለን፡፡ መጋቢት 21 ቀን 2004 ዓ.ም በወጣው ፍትህ ጋዜጣ በአቶ እስክንድር ነጋ ተሰጠ የተባለው ቃል እዚህ ችሎት ከቀረበው ጋር አንድ አይደለም፡፡ ዐቃቤ ህግ ነፃ ሆኖ እንደማይሰራ፣ በመንግስት ፖለቲካዊ ጫና መረጃ እንደሚፈበርክ ነው የተዘገበው። በነፃነት እየሰራን ሳለ አመኔታ እንዳይኖረን የሚያደርግ ዘገባ እየቀረበብን ነው”ብሏል።

ፍርድ ቤቱም፡- ዐቃቤ ህግ የፍርድ ቤት ዘገባን በተመለከተ በፕሬሶች  ላይ ያቀረበው አቤቱታ  መመዝገቡን በመጥቀስ፤ በተከሳሾች የተከሳሽነት ቃላቸው ላይ አቃቤ ህግ ያቀረበው አቤቱታ ግን አግባብ ባለመሆኑ እንዳልተቀበለው  ገልጿል፡፡

በዚህ ጊዜ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ተነስቶ፦” ክቡር ፍርድ ቤት፣ ፍትህ ጋዜጣ ላይ የቀረበው ቃሌ ምንም የተዛባ ነገር የለውም፡፡ ቃሌ ነው…”እያለ  መናገር ሲጀምር ፍርድ ቤቱ፦ በተግሳጽ መልክ “ተቀመጥ!” በማለት ምንም እንዳይናገር ከልክሎታል፡፡

 ፍርድ ቤቱም ጋዜጦቹን በወፍ በረር ከተመለከተ በኋላ የመሐል ዳኛ እንዳሻው አዳነ፣ የቀኝ ዳኛ ሙሉጌታ ኪዳኔ እና ዳኛ አራጋው በሪሁንን የተኩት የግራ ዳኛ  ሁሴን ይመር በመነጋገር ዐቃቤ ህግ በፍትህ ጋዜጣ የመጋቢት 21 እና የካቲት 30 2004 ዕትሞች እንዲሁም በነጋድራስ ጋዜጣ መጋቢት 21 ቀን 2004 ዓ.ም ዕትም  ዘገባዎች  ዙሪያ የጋዜጣዎቹ ዋና አዘጋጆቹ ቀርበው እንዲያስረዱ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

ዐቃቤ ህግም ያሰማውን  አቤቱታ በጽሑፍ እንዲያቀርብ  ፍርድ ቤቱ አዟል፡፡

የተከሳሾች የሰው ምስክር በመጠናቀቁም፤ የሰነድና ኦዲዮ ቪዥዋል ማስረጃዎችን ለማየት  ለሚያዚያ 3 ቀን 2004 ዓ.ም  ፍርድ ቤቱ  የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል።

________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide