መጋቢት ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- በአቶ መለስ ዜናዊ የሚመራው የኢህአዴግ መንግሥት የሕዝበ ሙስሊሙን የመጅሊስ ይውረድ፣ የአህባሽ አስተምህሮ በግዳጅ ላያችን ላይ አይጫንብን እና በሃይማኖታችን ላይ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ይቁምልን ጥያቄን ፖለቲካዊ ትርፍ ሊያገኝበት በሚችልበት መንገድ ለመፍታት እየሞከረ እንደሆነ ምንጮች አስታወቁ፡፡
በአቶ በረከት ስምዖን የሚመራው ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት፣ በፌዴራል ጉዳዮች ጽ/ቤትና ከደህንነት በተሰባሰበ መረጃ ቀደም ሲል በኢህአዴግ መንግሥት ከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ እንደ ማህበረሰብ እምብዛም የመንግሥት ተቀናቃኝ ያልነበረው የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ አሁን በመንግሥት ተማሯል፡፡
ስለዚህ የተቃውሞ ሁኔታውን ለመቀልበስ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ያዋቀራቸው 17 ኮሚቴዎች ለአቶ መለስ ጽ/ቤት ባስገቡት ደብዳቤ መሠረት ለሙስሊሙ ማህበረሰብ የመጨረሻ መፍትሄ አቶ መለስ ለመስጠትና ተወዳጅነትን በማትረፍ ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ሊያገኙበት እየተሰራ መሆኑን ምንጮች ለዘጋቢያችን አስረድተዋል፡፡
የሙስሊሙ ማህበረሰብ መጅሊስን ለማፍረስ ካዋቀራቸው ኮሚቴዎች አንዱ ለዘጋቢያችን እንደተናገሩት ባለፈው ዓርብ ለህዝበ ሙስሊሙ በአወሊያ እንደተናገሩት መንግሥት በአቶ ሬዲዋን ሁሴን በኩል ካለፈው ዓርብ ጀምሮ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ መፍትሄ እንደሚሰጥ አሳወቆ ታገሱኝ ማለቱንና በዚህ ጊዜ ውስጥ መፍትሄ ካልተሰጣችሁ ተቃውሟችሁን መቀጠል ትችላላችሁ ብሏል ብለዋል፡፡
ዓርብ መጋቢት 14 ቀን 2004 ዓ.ም በአወሊያ መስኪድ ከሦስት መቶ ሺህ የአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ሙስሊሞች ተሰብስበው እንደነበር ይታወሳል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide