በጋምቤላ የጸጥታ ማስጠበቁ ስራ ለፌደራል ፖሊስ ተሰጠ ምክር ቤቱም ተከፍሎአል

መጋቢት ፲ (አስር) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በጋምቤላ የጸጥታ ማስጠበቁ ስራ ከክልሉ መንግስት ተወስዶ ለመከላከያ እና ለፌደራል  ፖሊስ ተሰጠ  ምክር ቤቱም ተከፍሎአል

በጋምቤላ የሚታየው የጸጥታ መደፍረስ የመገናኛ ብዙሀንን ትኩረት ስቦ ቆይቷል። የኢሳት ዘጋቢዎች  በክልሉ ያለውን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ሲዘግቡና ለህዝብ ይፋ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

በኢትዮጵያ የምእራብ ጠረፍ የምትገኘዋ ጋምቤላ በስልጣን ላይ ያለው የህወሀት መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ ሰላምና መረጋጋት ርቋት ቆይቷል። ከ9 አመታት በፊት በክልሉ በተፈጠረ የዘር ግጭት የህወሀት / ኢህአዴግ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ የአኝዋክ ተወላጆችን መጨፍጨፋቸውን ጄኖሳይድ ወችን እና ሂውማን ራይትስ ወችን ጨምሮ ብዙ አለማቀፍ ድርጅቶች ሪፖርት አቅርበዋል።

በቅርቡ ደግሞ በክልሉ የሚኖሩ ሰዎች ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች መገደላቸው ጋምቤላ እንደገና የአለም የመገናኛ ብዙሀን አይን እንዲያርፍባት አድርጓል። ባለፈው ሳምንት 19 ሰዎች ተገድለው 8 ሰዎች መቁሰላቸውን የአለም የመገናኛ ብዙሀን ሽፋን ከማግኘቱ በተጨማሪ የአፍሪካ ህብረትም ድርጊቱን ኮንኗል። ግድያውን ማን እንደፈጸመው በውል ባልታወቀበት ወቅት ኢሳት ከግድያው ጀርባ የመንግስት እጅ ሊኖርበት እንደሚችል የሚጠቁም ዘገባ አቅርቦ ነበር።

ሰሞኑን ወደ ጋምቤላ የተጓዙት የአቶ መለስ ዜናዊ ልዩ የጸጥታ አማካሪ የሆኑት አለቃ ጸጋየ በርሄ፣  የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ ወርቅነህ ገበየሁና የህወሀት ከፍተኛ ባለስልጣናት ችግሩን ለመፍታት ላይ ታች ሲሉ ሰንብተዋል። ባለፈው አርብ  መጋቢት 7፣ 2004 ዓም የህወሀት ባለስልጣኖች የጋምቤላ ክልል ምክር አባላትን፣ የቀበሌ አመራሮችንና የመንግስት ሰራተኞችን ሰብስበው ባነጋገሩበት ወቅት የተሰነዘሩት አስተያየቶች በክልሉ ያለው ችግር ውስብስብ እየሆነ መምጣቱን የሚያመልክት ነው።

አለቃ ጸጋየ በርሄና ፕሬዚዳንቱ ኦመድ ኦባንግ በመሩት ስብሰባ ላይ የተነሱት ዋና ዋና ነጥቦች በክልሉ ፕሬዚዳንት የስልጣን እድሜና በክልሉና በፌደራል መንግስቱ መካከል ስላለው ግንኙነት የሚያተኩሩ ነበሩ።

አንድ የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣን ለፕሬዚዳንቱ ባቀረቡት አስተያየት ” ለአንተ የተሰጠው የስልጣን ጊዜ 6 ወር ነበር፣ አሁን ያ ቀን ከመድረሱ በፊት ስልጣንክን መልቀቅ አለብህ። በአንተ ምክንያት ነው ህዝብ እያለቀብንና እየተፈጀ ያለው። ከስድስት ወር በፊት ተነጋግረን ስልጣንክን ማስረከብ አለብህ። ለአንተ ሲባል የእኛ ልጆች መጨረስ የለባቸው። ” ብለዋል።

ሌላ ባለስልጣን ደግሞ ” አንተ ከፌደራል መንግስት ጋር በመመሳጠር የተለያዩ መሬቶችን ያለእኛ እውቅና ሸጠሀል። መሬቱ የሚቸበቸበው እኛ አኝዋኮች በማናውቀው መንገድ ነው። አንደኛው የችግር ምንጭም ይህ ነው” ሲሉ አክለዋል።

ውይይቱ እየጦዘ ሲመጣ ባለስልጣናቱ እርስ በርሳቸው ተከፋፈለው ነበር። አንዳንዶቹ ባለስልጣናት ” በህገ መንግስቱ አንመራም፣ ራሳችንን ችለን  ማስተዳደር ነው የምንፈልገው፣ ከፌደራል መንግስት ምንም አይነት ድጎማ አንፈልግም፤ ጁባ ራሷን ችላ እንደምትተዳደረው እኛም የፌደራል ጥገኛ ሳንሆን ራሳችንን ችለን እንተዳደራለን። የፌደራል መንግስት ጥገኞች በመሆናችን የተረፈን መሬታችንን በህገ ወጥ መንገድ መቸብቸብ ነው። ” የሚል አቋም በማራመዳቸው ባለስልጣናቱ ከሁለት ተከፋፍለው ይጠዛጠዙ ነበር።

በባለስልጣናቱ አቋም የተደናገጡት የፌደራሉ ባለስልጣናት ፣ እንዲህ አይነት አቋም የሚያራምዱ ባለስልጣናት ምናልባት ጸጥታ በማወክ በኩል እጃቸው ሳይኖርበት አይቀርም በሚል እንዲጣራ ወስነዋል።

የክልሉ መንግስት የጸጥታ ሁኔታውን ለመቆጣጠር ከአቅሙ በላይ በመሆኑ፣ የጸጥታ ስራን በተመለከተ ሀላፊነቱን መከላከያና ፌደራል ፖሊስ እንደሚወስደው ተገልጧል።

ቅዳሜ እለት ደግሞ አለቃ ጸጋየ፣ ወርቅነህ ገበየሁና ኦሞድ የሟች ቤተሰቦችን ለመጎብኘት ወደ ጎደሬ ማምራታቸው ታውቋል። ይሁን እንጅ ጎደሬ ሲደርሱ የጋምቤላ ክልል ባንዲራ ወርዶ በመቃጠል ላይ ነበር። ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው ምንጮች እንዳሉት ባንዲራው የተቃጠለው የፌደራል መንግስት ባለስልጣናት ወደ ስፍራው እንደሚሄዱ ከታወቀ በሁዋላ ነው።  

 ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ሰኞ በ19 ተማሪዎች ላይ የተፈጸመው ግድያ በክልሉ የተፈጠረው ውዝግብ  ውጤት መሆኑ ታውቋል። ከመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ግንኙነት በመፍጠር ግድያ ፈጽሟል የተባሉ የአኝዋክ ተወላጅ እንዲሁም የአቦቦ የጸጥታ ዘርፍ ሀላፊ የሆኑት አቶ ኡቻ በቁጥጥር ስር ውለዋል። አቶ ኡቻ የተያዙት ከተረፉ ሰዎች በተደረገ ጥቆማ ሲሆን ለአንድ ወር እረፍት ወስደው ይህን ስራ ሰርተዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል። አቶ ኦቻ ግድያውን ከሌሎች ባለስልጣኖች ጋር በመሆን ማስፈጸሙን አምኗል ተብሎአል። ይሁን እንጅ በኢትዮጵያ የወንጀል ምርመራ የተያዙ ሰዎች በሀይል ወንጀልም ሳይሰሩ እንዲያምኑ ስለሚገደዱ ፣ የእርሳቸው እምነት ከልብ የመጣ ይሁን ተገደው ለማወቅ አልተቻለም።

በክልሉ የሚኖሩ ሰዎች እርስ በርሳቸው መከፋፈላቸውን እና አለመተማመኑ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱ ታውቋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide