መጋቢት 7 ቀን 2004 ዓ/ ም
ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊ ት ወደ ኤርትራ ድንበር በመግባት በኤርትራ ወታደራዊ ተቋማትና ማሰልጠኛዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ማስታወቁን ተከትሎ ኤርትራ የኢትዮጵያ መንግስት የጸብ አጫሪነት እርምጃ የድንበር ኮሚሽኑ የሰጠው ውሳኔ 10ኛ አመት እየተቃረበ መምጣቱን ተከትሎ የአለማቀፍን ትኩረት ለማስቀየር ታልሞ የተደረገ መሆኑን ኤርትራ ገልጣለች።
የድንበር ኮሚሽኑ ባድመ ለኤርትራ ይገባል በማለት ከ10 አመታት በፊት ቢወስንም ኢትዮጵያ እስከዛሬ ለማስረከብ ፈቃደኛ አለመሆኑዋን የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የሆኑት አቶ አሊ አብዶ ገልጠዋል።
የህወሀት መንግስት በአገር ውስጥ እየተከተለ ያለው የዘር ፖለቲካ ሌሎችን ህዝቦች እያገለለ መምጣቱን ያወሱት አቶ አሊ፣ በዚህም የተነሳ የአገሪቱ መንግስት ለብዙሀኑ ህዝብ ባዳ የሆነ፣ የገዢዎቹ ቤተሰቦች ጥቅም ብቻ የሚያስከብር መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው የተቃውሞ ምንጭ ይህ የዘር ፖለቲካ የወለደው መሆኑን የተናገሩት ሚኒሰትሩ ፣ በዚህም የተነሳ ተቃውሞው በእየአቅጣጫው እየፈነዳ መሆኑን ገልጠዋል። የህወሀት መንግስትም የህዝቡን የትኩረት አቅጫጫ ለማስለወጥ እየሰራ መሆኑን ገልጧል።
ጦርነትን የሚራቡ የጦርነትን አስከፊነት ያልተረዱ ናቸው በማለት የተናገሩት አቶ አሊ፣ ህወሀት በድንበሩ አካባቢ የሰነዘረው ጥቃት በሌሎች አገሮች ድጋፍ የተካሄደ መሆኑንም ጠቁመዋል፤ ኤርትራ ለተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ባቀረበችው ደብዳቤ ላይ የመለስ መንግስት ድፍረት ምንጩ የአሜሪካ ድጋፍ ነው ብላለች።
ኤርትራ ለጥቃቱ አጸፋዊ ምላሽ ትሰጥ እንደሆን ሲጠየቁ ” አገራቸው ጦርነት የመዋጋት ፍላጎት እንደሌላት ፣ ይሁን እንጅ የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ እርምጃ እንዲወስድ መጠየቃቸውን ተናግረዋል።
የአለማቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ በወሰደችው እርምጃ ላይ የተለያዩ የአቋም መግለጫዎችን አውጥቷል።
የአውሮፓ ህብረት የዉጭ ጉዳዮችና የፀጥታ ፖሊሲ ከፍተኛ ሃላፊና የኮሚሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት ካትሪን አሽተን ቃል አቀባይ በሰጡት መግለጫ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል እያደገ የመጣዉ ዉጥረት በተለይም የኢትዮጵያ ወታደሮች የፈፀሙት ተግባር ህብረቱን በከፍተኛ ደረጃ እንዳሳሰበዉ ገልፀዋል።
ሁለቱም ወገኖች ከአመፅ ተግባር እንዲቆጠቡና በአለምአቀፍ ህግ አጠቃላይ ደንቦች እንዲመሩ እንዲሁም በአልጄርሱ ስምምነት የገቧቸዉን ግዴታዎች እንዲያከብሩ አሳስበዋል።
ህብረቱ በአፍሪቃ ቀንድ ፀጥታና መረጋጋት እንዲሰፍን ጠንካራ ፍላጎት እንዳለዉ በመግለፅ በተለያዩ ወገኖች መካከል በክልሉ ዉስጥ ያሉ ልዩነቶችን ለማስታረቅ ጥረት በሚደረግበት ወቅት ኤርትራና ኢትዮጵያ በመካከላቸዉ ለሚገኙና እልባት ላላገኙ ጉዳዮች በጋራ ግንኙነት መፍትሄ ለመፈለግ ጥረት ማድረግ እንደለባቸዉ አመልክተዋል።
በሌላ በኩል ይህንኑ የኢትዮጵያ መንግሰት የሰጠዉን ሪፖርት በተመለከተ የዩናይትድ ስቴትስ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ቪክቶሪያ ነላንድ ሁለቱም ወገኖች ቀጣይ ወታደራዊ እርምጃ ከመዉሰድ እንዲቆጠቡ በማስገንዘብ አገሮቹ ስላላቸዉ ሃሳብ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡ እንደሚጠየቁ ገልፀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የምታደርገውን ጦርነት እየተቃወም ነው።
በማህበራዊ የመገናኛ መድረኮች የሚወጡ ጽሁፎች ባብዛኛው እንደሚያሳዩት በውጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ከእንግዲህ ደም ፈሶ እንደማያዩ ይገልጣሉ።
ከአድማስ የተባሉ ሰው በፌስ ቡክ ባሰፈሩት ጽሁፍ “ሰወች ከልቤ ልንገራችሁ እመኑኝ መለስ እንኳን በውኑ በህልሙም አንድ ቀን እንኳ ተሳስቶ ለኢትዮጵያ አስቦ አያውቅም ለዚህም ስራው ምስክር ነው ከዚህም በጥቂቱ ኤርትራን ከናት አገሯ ከኢትዮጵያ አስገነጠሎ ኢትዮጵያን የምታህል ባለታላቅ የታሪክ ሃብታም የሆነች አገራችን ያለወደብ አስቀረ ፣ አባቶቻችን አገራችንን ለውጭ ባእዳን ላለማስደፈር ታቦት ይዘው የተዋጉላትን አገር ዛሬ ቤተክርስቲያናትን እያፈረሰ መሬቷን እየሸጠ ነው፣ ኧረ ስንቱ ተዘርዝሮ….ያም ሆነ ይህ መለስ የአገር መሪ መሆን ቀርቶ የቤተሰብ መሪ መሆን አይችልም ኢትዮጵያ ከ20ዓመት በላይ ያለመሪ የቆየች አገር ነች መለስ በአገራችን ለይ ያደረጋቸው ስምምነቶች ሁሉ የአገራችንን መብት እና ጥቅም ያላስከበሩ በህዝብ ስምምነት ያልፀደቁ ስለሆነ በእውነተኛ ኢትዮጵያውን ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት የላቸዉም።” ብለዋል።
አንድ ስማቸውን ያልገለጡ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው ዋናው አላማው ትኩረት ማስቀየር ነው: ወያኔ ተስፋ በቆረጠ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው። ከ20 አመት በሁዋላ ወያኔ ከማንም ጋር ሰላም መሆን አልቻለም። በአገሪቱ ውስጥ ያሉ አሳሳቢ ችግሮች መፈናፈኛ አሳጥተውታል። አገርን መምራት ጦር ወደ ባይደዋ ወይም አስመራ እንደመላክ ቀላል አይደለም። ባለፉት 10 አመታት የተከተሉት የተሳሳተ ፖሊስ አሁን ለተፈጠረው የገንዘብ ግሽበት እና የኑሮ ውድነት ምክንያት ሆኗል። በደርግ ጊዜ የተጀመረው ፍርሀት ቀስ በቀስ እየተሰበረ በመጣበት ወቅት ላይ ወያኔዎች በጣም ተደናግጠዋል። ስለዚህም የህዝቡን ትኩረት ለማስቀየር ኤርትራ ተሻግረው ባዶ መንደር ይደበድባሉ ሲሉ ጽፈዋል።
የመለስ መንግስት አሁን በኤርትራ ላይ ወረራ ቢያካሂድ ከ10 አመት በፊት እንደነበረው አይነት ህዝባዊ ድጋፍ እንደማያገኝ በሶማሊያ ካካሄደው ጦርነት በመነሳት መገመት እንደሚቻል አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide