የአለም ደቻሳ ጉዳይ በርካታ ኢትዮጵያውያንን እያስቆጣ ነው

መጋቢት 7 ቀን 2004 ዓ/ ም

ኢሳት ዜና:-በሊባኖሳዊው ጎረምሳ ከተደበደበች በሁዋላ እራሱን ያጠፋቸው አለም ደቻሳ በርካታ ኢትዮጵያውያንን እያስቆጣ ነው

በአዲስ አበባ ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው ሰዎች እንደገለጡት ድርጊቱ ኢትዮጵያኖች ያሉበትን የውርደት ደረጃ የሚያሳይ ነው። አለም ከኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ፊት ለፊት መደብደቡዋ ፣ ጉዳዩን አሳዛኝ ማድረጉን የገለጡት ነዋሪዎች፣ የኢትዮጵያ መንግስት የዜጎቹን ደህንነት በውጭ በሚገኙ ኢንባሲዎቹ አማካኝነት ካላረጋጋጠ ኢምባሲ መክፈት ለምን እንዳስፈለገም ጠይቀዋል።

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ለረጅም ጊዜ በአረብ አገራት የቆዩ ሴት ” በአረብ አገራት በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰው ውርደት፣ የአገር ውስጡ ውርደት ነጸብራቅ ነው። በአገር ውስጥ ብንከበር፣ እንደ ዜጋ ብንቆጠር፣ በውጭም እንከበር ነበር። ዛሬ በሀገራችን እንደሰው ሳንቆጠር እንዴት በባእዳን ዘንድ እንደ ሰው እንድንቆጠር ይጠበቃል ብለዋል።

ሌላ በአረብ አገር ሰራተኛ የሆነችና ቤተሰቦቹዋን ለመጠየቅ ወደ አዲስ አበባ የሄደች ወጣት ደግሞ ፤ አለም ከተደበደበች በሁዋላ ከኢትዮጵያ የቆንስላ ሀላፊ ጋር ተገናኝታ ነበር። ታዲያ እንዴት የቆንስላው ሃለፊ አለም ከአእምሮ ጉዳቷ ሳታገግም ዝም ብሎ ለብቻዋ ተዋት። ተጠያቂዎቹ በዚያ አገር የሚገኙ የቆንስላው ሰራተኞች ናቸው ስትል አስተያየቷን ገልጣለች።  ወጣቷ የአለም ደጃሳ ጉዳይ በአጋጣሚ ለአለም ይፋ ይሁን እንጅ ከዚህ የበለጠ ስንት ግፍ በኢትዮጵያ ሴቶች ላይ በሳውዲ፣ በየመንና በኪዌት ይፈጸማል ስትል አክላለች።

በአዲስ አበባ የሚገኙ ወጣቶች የሻማ ማብራት ስነስርአት ለማካሄድ እየተንቀሳቀሱ ነው። በርካቶች የኢትዮጵያ መንግስት የአለምን ደህንነት መጠበቅ ሲገባው፣ ከጉዳቷ በሁዋላ ዝም ብሎ ስለለቀቃት ተጠያቂ መሆን አለበት ይላሉ።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide