መንግስት የደሞዝ ጭማሪ አደረኩ ብሎ ቀለደብን ሲሉ መምህራን ተናገሩ
የኢትዮጵያ መምህራን የኑሮ ውድነቱ ልንሸከመው ከምንችለው በላይ በመሆኑ መንግስትን የደሞዝ ጭማሪ እንዲያደርግ ሲያሳስቡ ቆይተዋል። በደምቢያ፣ በደባርቅ እና በሌሎችም የሰሜን ጎንደር ትምህርት ቤቶች መምህራን የስራ ማቆም አድማ በማድረግ ለጥያቄያቸው መልስ እንዲሰጣቸው ግፊት አድርገዋል። የመምህራኑ የስራ ማቆም አድማ ዛቻ ያሰጋው መንግስት በትምህርት ሚኒስትሩ በአቶ ደመቀ በኩል ባለፈው ሳምንት ፤ መንግስት አጥጋሚ ምላሽ እንደሚሰጥ ተናግሮአል። መምህራኑም የሚኒስትሩን ቃል አምነው በትእግስት ለመጠባባቅ ወስነው ነበር። ከትናንትና በስቲያ መንግስት አደረኩት ያለው የደሞዝ ጭማሪ ግን፣ መምህራን ከተጠበቁትና ከገመቱት በታች ሆኖ አግኝተውታል።
አንድ ስማቸው እንዳይነገር የፈለጉ መምህር መንግስት ቀለደብን ሲሉ ተናግረዋል። መምህሩ የሚለው መምህሩ የመንግስት የመገናኛ ብዙህንን ዘገባም ነቅፈዋል መምህሩ 2 ከሚለው የመምህራንን ቅሬታ በአገር ውስጥ የሚታተሙትም ጋዜጦች የዘውት ወጥተዋል።
ሰንደቅ የተባለ ጋዜጣ አንዱን መምህርን ጠቅሶ እንደዘገበው ጭማሪው ለመምህራን ስድብ ነው። “አንድ ዲግሪ ለያዘ መምህር 73 ብር መጨመር ምን ማለት ነው?” በማለት የሚጠይቁት መምህሩ በአንዳንድ ኤሌክትሮኒክስ የመገናኛ ብዙሃን መምህሩ 5 ሺ እና 7 ሺ ብር ጭማሪ እንዳገኘ የሚያስመስል ዘገባ መተላለፉ የቤት አከራዮች ጭምር ዋጋ ለመጨመር እንዲነሳሱ የሚያደርግ ነው በማለት ድርጊቱን ኮንነዋል።
ሌላ የመምህራን ማኅበር አመራር አባል ጭማሪው የመምህሩን ጥያቄ በተሟላ መልኩ ያልመለሰ ነው ብለውታል። የእርከን ጥያቄያችን እንደሌሎች የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት 9 ድረስ ይሁን የሚል ነበር። ቀድሞ ስድስት ያህል የነበረውን በማስተካከያው ሰባት ሆኗል ነው የተባለው። መምህሩ ከሌላው የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኛ አንድ እርከን ከፍ ይል ነበር። ነገር ግን ሌሎቹ ከአራትና አምስት ዓመታት በኋላ በጭማሪ ከፍተኛ የሆነ ብልጫ ያሳያሉ። በዚህ ምክንያት ልዩነት እየተፈጠሪ በመሆኑ ጥያቄያችን ይሄ እንዲስተካከል ነበር ብለዋል።
ሪፖርተር ባወጣው ዘገባ ደግሞ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የማህበሩ አመራር አባላል በርካታ መምህራን ስልክ እየደወሉ ‹‹እንዴት በመንግሥት ታሰድቡናላችሁ?›› በማለት ብስጭታቸውን እየገለጹ ነው ብሎአል።
በአዲሱ የደሞዝ ጭማሪ አንድ የዲግሪ ምሩቅ 1 ሺ 644 ብር ያገኛል። ይህ አሀዝ በአዲሱ የኢትዮጵያ የኑሮ ሁኔታ ሲመነዘር አንድ ኩንታል ጤፍ እና 2 ኪሎ ስኳር ማንልባትም የተወሰኑ ሳሙናዎችን ይጨምራል። አሀዙ በዶላር ሲመነዘር የአንድ የዲግሪ ምሩቅ የወር ደሞዝ 96 ዶላር ነው። በደርግ ጊዜ የአንድ የዲግሪ ምሩቅ ደሞዝ 500 ብር የነበረ ሲሆን፣ በጊዜው በነበረው ምንዛሬ ወደ 150 ዶላር ይጠጋል። ይህ አሀዝ ቢያንስ በወር ከ5 ኩንታል ያላነሰ ጤፍ መግዛት ብቻ ሳይሆን ለቤት ኪራይና ሌሎችንም ወጭዎች ለመሸፈን ያስችላል። በአጼ ሀይለስላሴ ዘመን ደግሞ መምህራን የሚያገኙት ክፍያ በአንጻራዊ መልኩ ከፍ ያለ ስለነበር ” በሰርግ ዘፈን ሳይቀር የእኛ ሙሽራ ሹራብ ሰሪ፣ አገባች አስተማሪ” እየተባለ ይዘፈን ነበር። 11 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት እንዳገኘ በሚገልጠው የመለስ መንግስት መምህራን ከደርግ መንግስት በግማሽ ያነሰ ይከፈልላቸዋል።
የበርካታ መምህራን ስጋት ነጋዴው መምህሩ ብዙ ብር ያገኘ መስሎት የእህል እና የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ እንዳያደርግ ነው። የመምህራን በበቂ ሁኔታ ክፍያ አለማግኘት ቢኢትዮጵያ ውስጥ ለሚታየው የትምህርት ጥራት መሞት አስተዋጽኦ እንዳደረገ መምህራን ይናገራሉ።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide