የአፍሪካ መዲና በሆነችው በአዲስ አበባ የቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ መብራት ጠፍቶ በበረራ ላይ የነበሩ አውሮፕላኖች በጨላማ ሲያርፉ ማምሸታቸውን ዘግቧል።
ጋዜጣው ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ከትናንት በስቲያ ከቀኑ 11 ሰዓት እስከ ምሽቱ 2፡34 ሰዓት ድረስ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ የአውሮፕላን መንደርደርያዎች መብራቶች በመጥፋታቸው፤ አውሮፕላኖች በጨለማ ሲያርፉ አምሽተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ለዚህ አሰቃቂ ክስተት ተጠያቂው የኤርፖርቶች ድርጅት መሆኑን ተናግሯል፡፡
ለአውሮፕላን መንደርደሪያዎቹ መብራት መጥፋት ምክንያቱ፤ የኤርፖርቶች ድርጅት በማሠራት ላይ የሚገኘውን የአውሮፕላን ማቆሚያ፣ ማረፊያና ማኮብኮቢያ ማስፋፊያ ፕሮጀክት የሚሠራው የቻይናው የመንገድና ድልድይ ግንባታ ኮርፖሬሽን (CRBC)፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሩን ስለበጠሰው ነው ብለዋል-ምኝጮቹ።
በዚህም ሳቢያ አንድ አውሮፕላን ለማረፍ ዝቅ ሲል ቀይ፣ ከፍ ሲል ሰማያዊ እና ትክክለኛ አቅጣጫውን ሲይዝ ደግሞ ነጭ መብራት የሚያሳየው ፓፒ (PAPI) የሚባለው ብርሃን ሰጪ መሣርያ ጠፍቶ ነበር
እንዲሁም አውሮፕላኑ ከማረፊያ ሜዳው ያለውን ርቀት በማንበብ የሚያሳውቀው መሣሪያ (Distance Measuring Equipment) ጠፍቶ እንደነበር የገለጹት ምንጮቹ፣ አውሮፕላኖቹ በጨለማ ያርፉ የነበሩት ካርጐ ተርሚናል ውስጥ በነበረ አውሮፕላን ውስጥ የነበረ ፓይለት ብርሃን እያበራላቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ከዚህም በላይ አንድ አውሮፕላን ከአንድ አገር ተነስቶ ወደሚያርፍበት አገር እስከሚደርስ ድረስ የሚበቃውን ነዳጅ ከሞላ በኋላ፣ በሚያርፍበት አገር የተለያዩ አጋጣሚዎች ተፈጥረው ለማረፍ ባይችል፣ ለማረፍ በሚችልባቸው ቅርብ አገሮች ወይም ማረፊያዎች ድረስ የሚያደርሰውን ወይም በአየር ላይ የሚያቆየውን ተጨማሪ ነዳጅ መያዝ አለበት።
ሆኖም ይህ ችግር ሲፈጠር አውሮፕላኖቹ በጨለማ እንዲያርፉ የተደረገው፣ ምናልባት መጠባበቂያ ነዳጅ ስላልነበራቸው ሳይሆን እንደማይቀር ምንጮቹ ግምታቸውን ገልጸዋል፡
ያ ባይሆን ኖሮ ፤በቅርቡ ወደምትገኘው ጂቡቲ በመሄድ ማረፍ ይችሉ እንደነበርም አክለዋል፡፡
የኢትዮጵያውያን ፓይለቶች በአየር መንገዱ ለረጅም ዓመታት የሠሩና ለአውሮፕላን ማረፊያው እንግዳ ባለመሆናቸው፣ ያካበቱትን ልምድ ተጠቅመው በጨለማ ለማሳረፍ መቻላቸውን የገለጹት ምንጮቹ፣ አውሮፕላኑ የማረፊያ ሜዳውን ስቶ ቢያርፍ ችግር ይከተል እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በ25 ሺሕ ጫማ ከፍታ ላይ ጂቡቲን ጨምሮ በአገሪቱ ያሉትን አየር መንገዶችን የሚቆጣጠረው የአካባቢ መቆጣጠሪያ ማዕከልም ጠፍቶ ማምሸቱን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡
ስለጉዳዬ የተጠየቁት የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽንና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ፦‹‹በሕጉ መሠረት ወይም በዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ሕግ፣ መብራት ለ24 ሰዓታት መሥራት አለበት፡፡ ግዴታም ነው፡፡ ለማንኛውም አሁን ችግሩ ተፈትቷል፤›› በማለት ፣ በዋናነት ለችግሩ ተጠያቂው የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide