መጋቢት 1 ቀን 2004 ዓ/ ም
ኢሳት ዜና:-ቢቢሲ እንዳለው አልሸባብ፤ ሶማሊያ በሚገኘው የኢትዮጵያ ጦር ላይ ድንገት በከፈተው የማጥቃት እርምጃ በርካታ የኢትዮጵያ ወታደሮች መገደላቸውን ከአካባቢው የሚወጡ ሪፖርቶች ያመላክታሉ።
እንደ ዜና አውታሩ ዘገባ፤የኢትዮጵያና ጥቂት የሶማሊያ ወታደሮች የማዕከላዊ ጌዲኦ አካል በሆነችው በዩኩሩት ባለፈው ማክሰኞ ንጋት ላይ በአልሸባብ ተዋጊዎች ተከበቡ።
ከዚያም ለአራት ሰዓታት የዘለቀ ውጊያ ተካሄደ።
በሞቃዲሾ ሚገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ እንዳለው፤ የኢትዮጵያ ወታደሮች ባለፈው ህዳር ወደ ሶማሊያ ከገቡ ወዲህ እንደዚህ ዓይነት ከባድ ውጊያ አጋጥሟቸው አያውቅም።
የአልሸባብ ሚሊሻዎች ጥቃቱን የፈፀሙት፤ በኢትዮጵያ ጦር ላይ መንገድ ከዘጉና ጦሩን ወደ መሀል አስገብተው ዙሪያውን ከከበቡ በሁዋላ እንደሆነም ተመልክቷል።
“ሚሊሻዎቹ በኢትዮጵያ ጦር ላይ ጥቃቱን ከመፈፀማቸው በፊት ወደ ዩኩሩት የሚወስደውን መንገድ ዘግተው ነበር” ብሏል-የቢቢሲ ወኪል።
አልሸባብ ድንገት በከፈተው በዚህ የማጥቃት እርምጃ 73 የኢትዮጵያ ወታደሮችን እንደገደለ ሲገልጽ፤ የሶማሊያ መንግስት ደግሞ በውጊያው 48 የአልሸባብ አባላት መገደላቸውን ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጦራቸው የአፍሪካ ህብረትን ጦር በመተካት በመጪው ሚያዚያ ወር ከሶማሊያ እንደሚወጣ መናገራቸው ይታወሳል።
ባለፈው ማክሰኞ አልሻባብ በኢትዮጵያ ጦር ላይ ከበድ ያለ ጥቃት መፈፀሙ የዓለማቀፍ ታላላቅ መገናኛ ብዙሀን ዋና ርዕሰ-ወሬ በሆነበት ሰዓት የኢትዮጵያ መንግስት ስለ ጉዳዬ ምንም አለማለቱ ብዙዎችን አስገርሟል።
እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ 2006 ወደ ሶማሊያ ገብቶ የነበረው የ ኢትዮጵያ ጦር ከ 3 ኣመታት ቆይታ በሁዋላ ሲመለስ “በጦርነቱ ምን ያህል ወታደሮች ሞቱብን?” ተብለው በፓርላማው የተጠየቁት አቶ መለስ ዜናዊ፦ “በዚህ ደረጃ ለምክር ቤቱ ሪፖርት የማቅረብ ግዴታ የለብኝም” ማለታቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ጦር ባለፈው ህዳር ወደ ሶማሊያ ከመግባቱ ከሳምንት በፊት የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሴክሬታሪ ጆኒ ካርሰን፤ ኢትዮጵያ ጦሯን ወደ ሶማሊያ እንዳትልክ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።
አፍሪካን ሪቪው እንደዘገበው ደግሞ የኢትዮጵያ ጦር ባይደዋን በመቆጣጠሩ ንዴት ያደረባቸውና ራሳቸውን “ሙጃሂዲን” ብለው የሚጠሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ የውጪ አገር ዜጎች ከአልሸባብ አብረው የኢትዮጵያን ጦር ለመውጋት በኤደን ባህረ-ሰላጤ በኩል አድርገው ወደ ሶማሊያ እየገሰገሱ ነው።
ይሁንና “ሙጃሂዲኖቹ” ከየትኞቹ አገሮች የተውጣጡ እንደሆነ፤ በዘገባው ላይ አልተመለከተም።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide