“ዛሬ መሣሪያ የሌለው ጦርነት ውስጥ ነን” ሲሉ ኢ/ር ኃይሉ ሻወል ገለጹ

የካቲት 29 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የመ ኢአድ አባል የሆኑ አንድ አባት፤ ታማ የሞተች ልጃቸውን እንዳይቀብሩ ተከለከሉ።

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ ፕሬዝዳንት የሆኑት ኢ/ር ኃይሉ “ዛሬ መሳሪያ የሌለው ጦርነት ውስጥ ነን” ብለው የተናገሩት፤ 116ኛው የአድዋ ድል በዓል በፓርቲው ጽ/ቤት ሲከበር ነው፡፡

  ከዛሬ 116 ዓመት በፊት ጣሊያን ንቆን መጥቶ ተዋርዶ መመለሱንና  አያቶቻችን፤ ጥቁር ህዝቦች ሁሉ የሚኮሩበትን ገድል  አድዋ  ላይበማስመዝገባቸውን ያስታወሱት ኢንጂነር ሀይሉ፤ “በአፍሪካ ውስጥ ክብር ነበረን። እንደ ዛሬ የተናቅንበት ዘመን የለም፡፡ የንቀት ሹፈት እየተፈፀመብን ስለሆነ ክብራችንን ለማስጠበቅ መተባበር አለብን” ብለዋል፡፡

የመኢአድ ፕሬዚዳንት አክለውረም፦ ““ጣሊያን ሊከፋፍለን አልቻለም፡፡ የራስ ሰው ሊያታልል ስለሚችል ፤ዛሬ እያታለሉ  ይከፋፍሉናል።

ከእንግዲህ ግን መከፋፈልና መደበቅ የለብንም።በተለይ ወጣቱ ባይደበቅ ይሻለዋል፡፡ ምንም መደበቂያ ጫካ እንደሌለው አውቆ፤ መብቱን ጥቅሙን ለማስጠበቅና ነፃነቱን ለማስከበር መታገል ይጠበቅበታል፡፡” በማለት በተለየ መልኩ ለወጣቱ የትግልና የትብብር ጥሪ አቅርበዋል።

በተያያዘ ዜና  ኢህአዴግ በደቡብ ክልል የመኢአድ አባላት ላይ እየፈፀመ ያለውን የእስርና የማዋከብ  ዘመቻ  አጠንክሮ እንደቀጠለበት የድርጅቱ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ወ/ሪት መሶበ ቅጣው ገልጸዋል፡፡

ወ/ሪት መሰቦወርቅ እንዳሉት፤ ሰሞኑን በደቡብ ክልል ጐፋ ልዩ ዞን ደባ ጐፋ ወረዳ 4 አባላት በህገወጥ መንገድ የታሰሩ ሲሆን፤ በአምስት ቀበሌዎች  የሚገኙ 39  የመ ኢአድ አባላት ደግሞ  የሐሰት ክስ ተከሰው ፍ/ቤት እየተመላለሱ ናቸው፡፡

እንዲሁም  አቶ ዘነበ ዘዋ  የተባሉ የድርጅቱ አባል ባለቤት የሆኑ ሴት ፦“ባለቤትሽን ካላመጣሽ” ተብለው  በሚኒሻ እየተደበደቡ የ35 ደቂቃ መንገድ ከተወሰዱ በሁዋላ ባለቤታቸው ሲቀርቡ መለቀቃቸውን ወይዘሪት መሶበወርቅ ተናግረዋል።

እንደ ህዝብ ግንኙነት ሀላፊዋ ገለፃ፤ አቶ ጩንጋቹ ቡሌ የተባሉ ሌላው  የመኢአድ አባል ደግሞ  የሰባት ዓመት ልጃቸው ታማ እና አሳካሚ አጥታ ስትሞት በቀብሯ ላይ እንኳን እንዳይገኙ ተከልክለዋል፡፡

የዛላ ወረዳ  የመኢአድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ካሳዬ ከልስ  ደግሞ በፈጠራ ክስ ተከሰውና ዘጠኝ ወር ተፈርዶባቸው ማረሚያ  የወረዱ ሲሆን፤በ ኦይዳ ወረዳ ኡባ ያሞላል ቀበሌ ውስጥ ደግሞ ሌሎች 28 የ መ ኢአድ አባላት በፖለቲካ  አመለካከታቸው ብቻ የሐሰት ክስ ተመስርቶባቸው ፍርድ ቤት በመመላለስ ላይ መሆናቸውን ከወይዘሪት መሶበወርቅ ገለፃ ለመረዳት ተችሏል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide