ኢትዮጵያ የኮሜሳ ነፃ የንግድ ቀጣና አባል አገር ለመሆን ኢንዱስትሪያዊ ብቃት እንደሌላት ተገለፀ

የካቲት 21 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ኢትዮጵያ የምስራቅና የደቡባዊ አፍሪቃ የንግድ ቀጣና የጋራ ገበያ /ኮሜሳ /  ነፃ የንግድ ቀጣናዉ አባል ስለምትሆንበት ሁኔታ በቅርቡ በተደረገ ጥናት የአገሪቱ የማምረቻ ኢንዱስትሪ አለም አቀፍ ተወዳዳሪ የመሆን አቅም እንደሌለዉና መሻሻል እንደማይታይበት ፎርቹን ጋዜጣ ገለፀ።

ኮሜሳ ወጪዉን በሸፈነዉና የፋይናንስና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ያስተናበረዉን  ጥናት ያካሄደዉ መሰረቱን ዚምባብዌ ያደረገ ዚም ኮንሰልት የተባለ ገለልተኛ የኢኮኖሚና የፕላን አማካሪ ድርጅት ነዉ።

 ከአማካሪ ድርጅትና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተዉጣጡ ዶ/ር በክሪ ዩሱፍ፤ ዶ/ር ታደለ ፈረደ፤ ዶ/ር ወርቁ ገበየሁ ተሳታፊ የሆኑበትን የባለሙያ ቡድን ጥናት የመሩት የዚም ኮንሰልት ተወካይ ዳንኤል ኢንዴሊላ ናቸዉ።

የጥናቱ ዉጤት የተገለፀዉ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት ከጠቅላላዉ የአገር ዉስጥ ምርት 13.4 በመቶ ወደ ሁዋላ የቀረዉ የኢንዱስትሪዉ ዘርፍ ለብሄራዊዉ የኢኮኖሚ እድገት መሪነቱን ከግብርናዉ ዘርፍ እንዲወስድ ለማድረግ ፍላጎት እንዳለዉ በሚገልፅበት ወቅት ነዉ።

በቅርብ አመታት በኢንዱስትሪዉ መስክ አነስተኛ ለዉጥ ቢታይም አጠቃላይ ምርታማነቱ፤ ቴክኒካዊ ብቃቱ፤ ከተናጠል የምርት ዋጋ አመላካች መመዘኛዎች አንፃር በአለም ዝቅተኛ ተወዳዳሪ ከሚባሉት አንዱ እንደሆነ ጥናቱ አመልክቷል። 

የንግድ ሚኒስቴር፤ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፤ የኢትዮጵያ የገቢዎችና የጉምሩክ ባለስልጣን፤ የኢትዮጵያ የንግድ ምክር ቤትና በዘርፉ ያሉ ማህበራት፤ የኢትዮጵያ የደረጃዎች መዳቢ ባለስልጣን፤ የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ስብሰባ ላይ ጥናቱን ያካሄዱት ባለሙያዎች የኢንዱስትሪዉ ዘርፍ ያሉበትን ችግሮች በዝርዝር አቅርበዋል።

የፋይናንስ አለመኖር፤ከፍተኛ የማምረቻ ዋጋ፤ ዝቅተኛ የሆነ ምርታማነት የዘርፉ አቢይ ችግሮች መሆናቸዉ ሲገለፅ፤ የጥሬ እቃዎች እጥረትና ዝቅተኛ የጥራት ደረጃ፤ አነስተኛ የሆነ የሙያ ደረጃ፤ አሳሳቢ የሆነ የዉጭ ምንዛሬ እጥረት እና ተደጋጋሚና የተለመደ የኤሌክትሪክ ሃይል መቋረጥ የዘርፉ አይነተኛ ችግሮች መሆናቸዉ ተዘርዝሯል።  

የኮሜሳ አባል አገሮች ከ20 አመት በፊት በመሰረቱት ነፃ የንግድ ቀጣና ዉስጥ ኢትዮጵያ አባል መሆን ትችል እንደሆን የፖሊሲ ዉሳኔ ለመስጠት እንዲረዳ የተካሄደዉ ይህ ጥናት አገሪቱ ግብፅን፤ እና ኬንያን ከመሳሰሉ ክልላዊ የኢኮኖሚ ሃይሎች ጋር ተወዳዳሪ ሆና መቀጠሏን ለማረጋገጥ እንደነበር ታዉቋል።

 እንደኢንዱስትሪ ባለሙያዎቹ አስተያየት የኢትዮጵያ የነፃ የንግድ ቀጣናዉ አባል መሆን ደካማ የሆነዉን የኢንዱስትሪዉን ዘርፍ አደጋ ዉስጥ ሊጥለዉ ይችላል።

ከዚህ በፊትም ተመሳሳይ ጥናት ተደርጎ ኢትዮጵያ በገበያዉ ዉስጥ ሊኖራት የሚችለዉ የተወዳዳሪነት አቅም ደካማ እንደሆነ ተረጋግጦ እንደነበር ፎርቹን አመልክቷል። 

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide