የካቲት 19 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በአካባቢው መሬት በመውሰድ በእርሻ ሥራ ላይ የተሰማራ ወጣት ሰሞኑን ተገደለ።
በሊዝ ኪራይ በጣም ሰፊ መሬት በመውሰድ በእርሻ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሦስት ወጣቶች ፤እርሻቸውን ጎብኝተው ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች የተኩስ እሩምታ በመክፈት አንድኛውን ገድለውና አንድኛውን ክፉኛ አቁስለው ከአካባቢው ተሰውረዋል።
ከስፍራው የደረሰን ተጨባጭ መረጃ እንደሚያመለክተው፤መኪናው ውስጥ ከነበሩት ሶስት ወጣቶች መካከል አንድኛው ምንም ጉዳት ሳይደርስበት ከጥቃቱ ተርፏል።
የሟቹ ወጣት አስከሬን፤ ቤተሰቦቹ ወደሚገኙበት ወደ መቀሌ ከተማ ተልኮ የቀብር ሥነ-ስርዓቱ የተፈፀመ ሲሆን፤ክፉኛ የቆሰለው ወጣት ደግሞ በአዲስ አበባ ህክምና እየተከታተለ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጋምቤላ ድንገት በተወሰዱ ተመሣሳይ ጥቃቶች ሁለት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እንደተገደሉ መዘገባችን ይታወሳል። የህወሃት አባል በመሆን በክልሉ ለረዥም ዓመታት በምስጢር የደኅንነት ሠራተኛነታቸው የሚታወቁት አቶ ጌታቸው አንኮሬ ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች በተደጋጋሚ በጥይት ተደብድበው የተገደሉት፤ጥር 24 ቀን 2012 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ በክልሉ ፕሬዚዳንት በአቶ ኦሞት ኦባንግ መኖሪያ ቤት ውስጥ ስብሰባ ላይ ቆይተው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ነበር።
ሰሞኑን ደግሞ ኦባንግ አማው የተባሉ የጋምቤላ ልዩ ኃይል አመራር መኮንንና አንድ ሌላ የፖሊስ አባል ሲገደሉ፤ ንብረትነቱ የሼክ መሐመድ ሁሴን አላሙዲ የሆነው ሳዑዲ ስታር እርሻ ልማት ኩባንያየፋይናንስ ኃላፊና ሾፌራቸው መቁሰላቸው ተዘግቧል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጋምቤላ ፕሬዚዳንት አቶ ኦሞት መኖሪያ ቤታቸው ማደር ማቆማቸውና የክልሉ ባለሥልጣናትም መታጀብ መጀመራቸው ታውቋል።
በክልሉ ውጥረት ከወረዳ ወደ ወረዳ እየተስፋፋ ነው። የጋምቤላ ክልል ባለሥልጣናትን፣ ኢንቨስተሮችንና የህወሃት/ኢህአዴግን አገዛዝ ስላስጨነቀው ተደጋጋሚ ጥቃት እስካሁን በግልጽ ኃላፊነቱን የወሰደ አካል አልተገኘም።
አገዛዙም ሆነ የክልሉ አመራሮች ፤እስካሁን ለተካሄዱት ጥቃቶች ምንም ዓይነት ማስተባበያ አልሰጡም።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide