ጥር 24 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- “አገራችንን ከወድቀት ለማዳንና አንድነቷን አስጠብቆ ለማስቀጠል አሁኑ ተነስተን በጽናት እንታገል” ሲል አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ጥሪ አቀረበ።
“አገርን ከውድቀት መታደግ፤የወቅቱ አንኳር ጥያቄ ነው”በሚል ርዕስ አንድነት ባወጣው መግለጫ፤
“ከሦስት ሺህ ዓመታት በላይ በህልውናዋ ፀንታ የቆየችውን ይህችን አገር የዛሬዎቹ የኢህአዴግ ካድሬዎች
ሲሸራርፏትና ለባዕዳን አሳልፈው ሲሸጧት ፤እጃችንን አጣምረን ዳር ቆመን ልንመለከት አይገባም” ብሏል።
ኢህአዴግ የህልውናው እስትንፋስ አድርጎ በሚቆጥረው ህገ መንግሥት አንቀጽ 39 ላይ የሰፈረውን ሀሳብ ለማሳካት፤ከኤርትራ መለየት በኋላ ቀሪውን የኢትዮጵያ ግዛት በብሄረሰብ ሸንሽኖ ለመነጣጠል ያደረገው ሙከራ፤ በ1997ዓ.ም ምርጫ ወቅት መራጩ ህዝብ ባሳየው ፍጹም ኢትዮጵያዊነት ሳይሳካለት ቀርቷል ብሏል-አንድነት።
“አቶ መለስ ስልጣን እንደጨበጡ የባንዲራችንን ታሪካዊነትና ኢትዮጵያዊ ቅርስነት በማንቋሸሽ ከተራ የዱቄት መቋጠሪያ ጨርቅ እንደማይለይ አድርገው መናገራቸው፤ አገራችን፤ እንደ አገር በልበ-ሙሉነት እንዳትቀጥል ገና ከማለዳው የወጠኑት ስልት መሆኑን መረዳት አያዳግትም” ሲልም የኢህአዴግ ጸረ-ኢትዮጵያዊነት፤ ከሁዋላ ታሪኩ ጋር ተያይዞ የመጣ መሆኑን አውስቷል-አንድነት በመግለጫው።
“ከምርጫ 97 በኋላ ራሱን በመንግስትነት ሰይሞ ቤተመንግሥት የከተመው ኢህአዴግ፤ ነፃና
ፍትሐዊ ባልሆነ ምርጫ በ99.6 በመቶ ድምጽ ተመርጫለሁ ብሎ ሥልጣን መያዙን ዓለም የሚያውቀው ነው”ያለው አንድነት፤ “አምባገነናዊ ባህሪው ከዓመት ዓመት እየጨመረ የመጣው ይህ የገዥዎች ቡድን፤ በዘር ከፋፍሎ የኢትዮጵያን አንድነት ለማዳከም የቀየሰው ስትራቴጂና የወጠነው ሴራ ባለመሳካቱ፤ ደም የተከፈለበትን የአገሪቱን መሬት በበቆሎ ዋጋ እየቆረሰና እየሸነሸነ ለባዕዳን መቸርቸር ከጀመረ ሰነባብቷል” ብሏል።
ኢህአዴግ ከጎንደርና ከጋምቤላ ሰፋፊ መሬቶችን፦” የሱዳን ግዛት ነው” በሚል ቆርሶ በመስጠቱ ሣቢያ፤ “የአገሬን መሬት አላስነካም” ያለው ኢትዮጵያዊ ቦታውን ላለመልቀቅ እስከዛሬ አሻፈረኝ እንዳለ እንደሚገኝ የጠቀሰው አንድነት፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ዳግሞ የሚያርሰው መሬት ጠቦት በድህነት እየዳከረ ካለው የሰሜን ኢትዮጵያ ህዝብ በኢንቨስትመንት ስም ያችኑ ይዞታውን እየነጠቀ ለሳዑዲ አረቢያና ለህንድ ሀብታሞች መቸብቸቡን ተያይዞታል ብሏል።
በትዕቢት የተሞላው ኢህአዴግ በዚህ ዙሪያ የአገሪቱ ምሁራን በወቅቱ የሰጡትን አስተያየት ሲያጣጥል ቆይቶ፤ አሁን ደግሞ አለም አቀፍ ውግዘትንም እያስተናገደ ነው ብሏል-አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ።
“ውድ ኢትዮጵያውያን፣ እውን አገራችሁን ትወዳላችሁ? ኢትዮጵያ ቤታችሁ፣ ገመናችሁ፣ ትዳራችሁ፣
ህልውናችሁ እንደሆነች ይሰማችኋልን?”በማለት የሚቀጥለው የአንድነት መግለጫ፤ በ እርግጥ አገራችንን የምንወዳት ከሆነ፤ኢህአዴግ የኢትዮጵያን መሬት እየቆረሰ ለባዕዳን ሲያድል ዝምታችን ምን የሚሉት ነው?” ሲል አጠንክሮ ይጠይቃል።
“ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ” እንዲሉ፤ኢህአዴግ ይህን ድርጊት በማናለብኝነት እየፈጸመ ያለውም የኢትዮጵያን ህዝብ በመናቁ እንደሆነም አንድነት ጠቁሟል።
አንድነት አያይዞም፦ “ኢህአዴግ ዝምታችንን ከፍርሃት ስለቆጠረውም፤ ከአያት ከቅድመ አያት የወረስነውን ይዞታችንን ሊቀማን የእያንዳንዳችንን በር እያንኳኳ ነው”ብሏል።
“ በነዚህ ሦስት እና አራት ዓመታት ውስጥ፤ የኑሮ ውድነቱና የህዝቡ ድህነት መላ ካልተበጀለት፤ አገሪቱ አስፈሪ የሆነ የመበታተን አደጋ ሊያጋጥማት እንደሚችል” ኢህአዴግ ራሱ በህዳር 2004 ዓ.ም ለተማሪዎችና ለመምህራን ውይይት ባዘጋጀው ሰነድ ላይ በግልፅ እንዳስቀመጠው፤ አንድነት አውስቷል።
“ ኢህአዴግ የአገዛዝ ዘመኑን ለማራዘም ሲል የአገሪቱን ህልውና እየናደ መሆኑን ልብ ልንል ይገባል” ያለው አንድነት፤ “ኢትዮጵያን ከመበታተን ለመታደግና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነቷን ጠብቆ ለማቆየት መነሳት የሚገባን አሁን መሆኑን ተገንዝበን በፅናት ልንታገል ይገባል”ሲል የአሁኑኑ እንነሳ የትግል ጥሪ አቅርቧል።