ጥር 23 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በቻይና መንግስት በ200 ሚሊዮን ዶላር በተገነባው አዲሱ የአፍሪካ ህብረት ጽህፈት ቤትና አዳራሽ ቅጥር ግቢ ውስጥ የዓፄ ሀይለሥላሴ ሐውልት አለመቆሙ፤ በኢትዮጵያ የታሪክ ምሁራን ዘንድ ቅሬታና ተቃውሞ አስነሳ።
ቻይና- ለአፍሪካ ህብረት እንደ ገጸ-በረከት በነፃ ገንብታ ባስረከበችውና ባለፈው ሳምንት የመሪዎቹ ጉባኤ ሲካሄድ ተመርቆ በተከፈተው ታላቅ ህንፃ ውስጥ፤ከፓን አፍሪካኒዝም ሀሳብ አራማጆቹና ከአፍሪካ አንድነት መስራቾቹ ቀደምት የአፍሪካ መሪዎች መካከል ሐውልት የታነፀላቸው፤ የጋናው ኑዋሜ ክሩህማን ብቻ ናቸው።
ሐውልት የታሪክ ምልክት እስከሆነ ድረስ፤በህብረቱ ጽህፈት ቤት ሐውልት መቆሙ ካልቀረ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረት ከፍተኛውን ሚና ተጫውተዋል የሚባሉትን የኢትዮጵያውን አፄ ሀይለሥላሴን፤ የግብጹን ጋማል አብድል ናስርን፣ የሊቢያውን ሙአመር ጋዳፊንና የጋናውን ንዋሜ ክሩህማንን ያካተተ አንድ ሀውልት ቢታነጽ፤ ታሪኩን ሙሉና ሚዛናዊ ያደርገው እንደነበር ኢትዮጵያውያን ምሁራን ይናገራሉ።
በተለይ አዲስ አበባ ውስጥ በተገነባው የህብረቱ አዳራሽ ውስጥ የታነፀው ሐውልት፤ የህብረቱን ጽህፈት ቤት አዲስ አበባ እንዲሆን አስደርገው ግንባር ቀደም ትግል ሲያደርጉ የነበሩትን ቀዳማዊ ሀይለሥላሴን መዘንጋቱ ፤ቁራጭ እውነትን በመስጠት ታሪክን እንደማዛባት ነው ያሉት ምሁራኑ፤ ይህ የሆነበት ምክንያት ሊገባቸው እንዳልቻለም ተናግረዋል።
በዚህ ዙሪያ ቅሬታቸውን ከገለጹት ምሁራን መካከል ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴና ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ይገኙበታል።
ፕሮፌሰር ባህሩ፦” በአዲሱ የአፍሪካ ህብረት ህንፃ የንዋሜ ክህሩማንን ሐውልት ብቻ ማቆሙ ፤ለኔ ትርጉሙ አልገባኝም” ነው ያሉት።
ፕሮፌሰር መስፍን ደግሞ፦” ዓፄ ሀይለሥላሴ ያን ጊዜ ባይኖሩ ኖሮ፤ የአፍሪካ ህብረት አሁን የያዘውን ቅርጽ ሊይዝ አይችልም”ብለዋል።
ሁለቱም ምሁራን ዓፄ ሀይለሥላሴ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መቋቋምና በህይወት መኖር ከማናቸውም መሪዎች በላይ ያደረጓቸውን አስተዋጽኦ በማብራራት፤ ለንዋሜ ክሩህማን ሀውልት ታንፆ -ሀይለሥላሴ መረሳታቸው እጅግ እንዳስገረማቸው ተናግረዋል።
ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉት የኢሳት ምንጮች ግን፤ የዓፄ ሀይለ ሥላሴ ሐውልት እንዲቆም ያልተደረገው ፤አቶ መለስ ሀሳቡን በመቃወማቸው እንደሆነ ጠቁመዋል።
“አቶ መለስ በኢትዮጵያ ታሪክ “ታላቅ መሪ” የመባል በልጓም የማይገታ ልቅ ምኞት አላቸው” የሚሉት ምንጮች፣ ያለፉ የኢትዮጵያ ነገሥታት መልካም ታሪኮችን የማጥፋትና የማጉደፍ ተግባር ላይ ሆነ-ብለው የተሰማሩትም፤ ከዚህ ‘የግል ስሜታቸው’ በመነሳት ነው” ብለዋል።
በተለይ የዓፄ ሀይለስላሴ ሐውልት በህብረቱ ፅህፈት ቤት መቆሙ፤ህወሀት ከፍ ያለ ገንዘብ መድቦ የራሱን አዲስ ታሪክ ለማፃፍ የጀመረውን እንቅስቃሴ በተወሰነ ደረጃም ሊያበላሽበት እንደሚችል ይገመታል።
በመማሪያ መፃህፍት የፊት ገጾች ከሚወጡት ፎቶግራፋቸው በተጨማሪ በሚሊዮን በሚቆጠር ገንዘብ በቁልፍ መያዣዎችና በቢል ቦርዶች ላይ ፎቶግራፋቸውን እያሰራጩ ያሉት አቶ መለስ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በካድሬዎቻቸው፦”ዓባይን የደፈረ መሪ”የሚል ቅስቀሳ ማስነገራቸው ይታወቃል።