ጥር 23 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የአውራምባ ታይምሱ ማኔጂንግ ኤዲተር የነበረውና በቅርቡ በደረሰበት ጫና ለስደት የተዳረገው ጋዜጠኛ ዳዊት ይህን የተናገረው፤ ሰሞኑን የአቶ መለስ ፍርድ ቤት በነ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ላይ ፍርድ መስጠቱን ተከትሎ -ከህብር ሬዲዮ ጋር ባደረገው ቃለ-ምልልስ ነው።
በ አንድ ችሎት ላይ ውብሸት ፍርድ ቤት ሲቀርብ ጆሮው ሲደማ መመልከቱንና ይህ የሆነውም በደረሰበት ድብደባ መሆኑን እንደተረዳ የገለጸው ጋዜጠኛ ዳዊት፤ ከዚያ ሁሉ በሀይል የታገዘ ምርመራ በሁዋላ ግን፤ለ 14 ዓመት ቀርቶ ለ 14 ቀንም ሊያሳስረው የሚያስችል መረጃ ሊያገኙ እንዳልቻሉ ጠቁሟል።
ሆኖም፤ጥፋት ስለፈፀሙ ሳይሆን ፤ከሥርዓቱ ባህሪ አኳያ እነ ውብሸት በነፃ ይለቀቃሉ የሚል እምነት ወትሮም እንዳልነበረው የጠቀሰው ጋዜጠኛ ዳዊት፤ ይሁንና ዐቃቤ ህግ ካቀረበባቸው ውሀ ከማይቋ ጥር መረጃ አንፃርም ፤ይህን ያህል ዓመት ይፈረድባቸውዋል ብሎ እንዳልጠበቀ ገልጿል።
ፍርድ ቤቱ በነ ውብሸት ላይ የ 14 ዓመት እስርና የገንዘብ ቅጣት ለማስተላለፍ እንደ ዋነኛ ጥፋት አድርጎ የጠቀሰው ምክንያት፤ “ጋዜጠኛ ኤልያስ ክፍሌ በዚህ በዚህ ቦታ ላይ በቃ ተብሎ የተፃፈውን ፎቶ አንስታችሁና ስካን አድርጋችሁ ላኩልኝ ያላቸውን ፈፅመዋል”የሚል እንደሆነ ዳዊት አስታውሷል።
“በዚህ ሳቢያ በጋዜጠኛ ላይ የ14 ዓመት እስራት መወሰን፤ የሰዎቹን ማንአለብኝነትና የደረስንበትን አሣሳቢ ደረጃ ያሳይ ካልሆነ በስተቀር ፤ምን ሊባል እንደሚችል አላውቅም” ሲልም ዳዊት አግራሞቱ መግለጹን፤ዋና ስቱዲዮው በላስ ቬጋስ የሚገኘው ህብር ራዲዮ ዘግቧል።
“ይገርም ነበረው አንድ ጋዜጠኛ “በቃ” የሚል ጽሁፍ መፃፉን ሰምቶና አይቶ ፎቶ ባያነሳውና ዝም ብሎ ቢያልፈው ነበር” ያለው አንድ ስሙን ያልጠቀሰ ጋዜጠኛ፤ “በነ ውብሸት ላይ በዚህ ምክንያት ሳቢያ የተላለፈው ፍርድ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በጋዜጠኝነት ሙያ ለመሰማራት የተጋረጠው አደጋ ከመቼውም ጊዜ በላይ የከፋና አሣሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ነው “ብላል።