ጥር 22 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ መንግሰት ወታደሮች የአልሸባብ ተዋጊዎች ጠንካራ ምሽግ ወደ ሆነዉ ቁልፍ አካባቢ በመግባት አዲስ የዉጊያ ቀጣና በመክፈት ላይ እንዳሉ የአይን ምስክሮች ገልፀዋል።
ዶሎዉ በተባለዉ የድንበር ከተማ በኩል ወደ ሶማሊያ የገባዉ የኢትዮጵያ ጦር በደቡብ ምእራብ ጌዶ ክልል ወደ ሚገኘዉ ለክ ከተማ እንዲሁም ባይ እና ባኩል ወደ ተባሉት በአልሸባብ ቁጥጥር ስር ወደሚገኙት አካባቢዎች እንዳመራ ታዉቋል።
በኢትዮጵያ ፤ በኬንያ እና በዋና ከተማዉ ሞቃዲሾ በተሰማራዉ የአፍሪቃ ህብረት ወታደሮች አልሸባብ በሶማሊያ ከፍተኛ ጫና እንደተፈጠረበት ይታወቃል።
ከአልቃይዳ ግንኙነት እንዳለዉ የሚገለፀዉ አልሸባብ ባለፈዉ ሳምንት በለደ-ወይን በሚገኝ ወታደራዊ ካምፕ ላይ በወሰደዉ የአጥፍቶ መጥፋት እርምጃ 33 የኢትዮጵያ ወታደሮች መግደሉን ገልጿል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚደገፈዉን የሶማሊያ የሽግግር መንግሰት ከስልጣን በማስወገድ በእስላማዊ ህግ የሚመራ መንግሰት ለመመስረት የሚዋጋዉ አልሸባብ በደቡብና በማእከላዊ ሶማሊያ ሰፊ አካባቢዎችን እስከቅርብ ወራቶች ድረስ ተቆጣጥሮ እንደነበር ይታወሳል።
በ18ኛዉ የአፍሪቃ የመሪዎች ሰብሰባ ላይ ለመገኘት አዲስ አበባ የሚገኙት የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሃፊ ባንኪ ሙን ከአሜሪካን ድምፅ ጋዜጠኛ ፒተር ሀይላይን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አልሸባብ በማድረግ ላይ ያለዉን ማፈግፈግ በመጠቀም የሱማሊያ መንግስት በጦርነት የተጎዳዉን አብዛኛዉን አካባቢ ገፍቶ በመቆጣጠር ይዞታዉን ማስፋት እንደሚገባዉ አሳስበዋል።