ጥር 21 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንደገለጡት በጥር ወር ጤፍ በተለምዶ የሚቀንስ ቢሆንም፣ በዚህ አመት ግን ይህ አልሆነም።
ሰሞኑን በምግብ እህል ላይ ከ50 ብር ያላነሰ ጭማሪ ታይቷል። የጤፍ ዋጋ በአማራ ክልል የተለያዩ ከተማዎችም ከ950 ጀምሮ በመሸጥ ላይ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ደግሞ ከ1 ሺ 100 ብር ጀምሮ እየተሸጠ ነው።
ወትሮውኑ በቆሎ እስከ 400 ብር በመሸጥ ላይ የነበረ ሲሆን፣ ሰሞኑን ከ500 ብር ጀምሮ በመሸጥ ላይ ነው።
በደቡብ ክልልና በድሬዳዋም የኑሮ ውድነቱ መባባሱን ዘጋቢዎቻችን ገልጠዋል።
የእህል ዋጋ ብቻ ሳይሆን የስኳርና ዘይት ዋጋም እንዲሁ ንሯል። ቀድሞ መንግስት በየቀበሌው በማከፋፈል ዋጋ ለማረጋጋት የሞከረ ቢሆንም እስከ መጨረሻው ግን ሊገፋበት አልቻለም። በዚህም የተነሳ ስኳር ተመልሶ ከገበያ ጠፍቷል።
የህዝቡ የገቢ መጠን እያሽቆለቆለ፣ የኑሮ ውድነቱ እየጨመረ መሄድ በአሜሪካና በአውሮፓ የሚታዩትን ወል ስትሪትን መውረር የሚለውን እያስታወሰን ነው ሲሉ አንድ ምሁር ተናግረዋል።
የሰሞኑ የኑሮ ውደነት ምናልባትም በኤርትራ ላይ የጦርነት ነጋሪት ከሚጎሰመው ጋር ሊያያዝ ይችላል ሲሉ ዘጋቢዎቻችን ይገልጣሉ።
ይሁን እንጅ ሰሞኑን አርሶአደሮች በማዳበሪያ እዳና በመሬት ግብር እየተዋከቡ መሆናቸው የዋጋ ውድነቱን አባብሰውት ሊሆን እንደሚችል ለኢሳት የደረሱት መረጃዎች ያመለክታሉ።
ሰሞኑን መንግስት በጀመረው የማዋከብ ዘመቻ፣ ራሳቸውን ማስተዳዳር የተሳናቸው እና በምግብ ለስራ ወይም ሴፍቲ ኔት የታቀፉ አርሶአደሮች ሳይቀሩ ማዳበሪያ ሳይወስዱ እንደወሰዱ እየተደረገ እዳ እንዲከፍሉ እየተገደዱ መሆኑን በአማራ ክልል የሚገኝ የአንድ ወረዳ የኢኮኖሚ ዘርፍ ሀላፊን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።
መንግስት ለአምስት አመቱ የልማት መርሀግብር ብዙ ገንዘብ ያስፈልገዋል በሚል ምክንያት የኢህአዴግ ካድሬዎች ገበሬው ጥሪቱ ሁሉ አሟጦ እንዲሸጥ እያስጨነቁት እንደሚገኝ ሀላፊው ለዘጋቢአችን ገልጠዋል።
የአለማቀፍ የገንዘብ ድርጅቶችና አክሰስ ካፒታል በቅርቡ ባወጡት ጥናት ለዋጋ ንረቱ አይነተኛው ምክንያት ገንዘብ ገበያው ሊሸከመው ከሚችለው በላይ በመታተሙ ነው።
ኢትዮጵያ በአለም ላይ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ግሽበት ካለባቸው ከሶስት አገሮች መካከል አንዷ ናት።