ጥር 16ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በህጋዊ ፓርቲ ጥላ ስር ተከልለው የመንግሥት ባለስልጣናትን ለመግደል፣ መሠረተ ልማቶችን ለማውደም እና ከአሸባሪ ቡድኖች ጋር አንድ ላይ በማበር ሕገመንግሥቱንና ሕገመንግሥታዊውን መንግስት ለመገልበጥ በሀገር ውስጥና በውጭ አገራት አሲረው ተንቀሳቅሰዋል ሲል የከሰሳቸው 24 የፖለቲካ ፓርቲ የአመራር አባላት፣ ጋዜጠኞች እና ነፃ አሳቢ ዜጎች ላይ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ትናንት የጥፋተኝነት ብይን ሰጥቷል::
ዘጋቢያችን እንደገለጠው ዐቃቤ- ህግ ካቀረባቸው ስድስት ክሶች ውስጥ በ1ኛ፣ በ2ኛ እና በ4ኛ ክሶች ላይ ተከሳሾች ጥፋተኛ ተብለው እንዲከላከሉ ብይን የሰጠው ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ፣ በ3ኛ እና በ5ኛ ክስ ዐቃቤ- ህግ በቂ መረጃ ባለማቅረቡ ከክሱ መከላከል ሳያስልጋቸው ነፃ ናቸው ብሏል፡፡
ፍርድ ቤቱ በ1ኛው ክስ በሀገር ቤት በእስር ላይ የሚገኙት ከ1ኛ እስከ 8ኛ ያሉ ተከሳሾች አንዷለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንን፣ ዮሐንስ ተረፈ፣ ሻምበል የሸዋስ ይሁንአለም ፣ ክንፈሚካኤል ደበበ፣ ምትኩ ዳምጤ፣ እስክንድር ነጋ እና አንዷለም አያሌው ክሱን እንዲከላከሉ ብይን የሰጠ ሲሆን፣ ከአገር ውጪ የሚገኙት 9ኛ ተከሳሽ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ 10ኛ ተከሳሽ ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ፣ 11ኛ ተከሳሽ ውቤ ሮቤ ፣ 13ኛ ተከሳሽ መስፍን አማን፣ 14ኛ ተከሳሽ ዘለሌ ጸጋ ስላሴ፣ 15ኛ ተከሳሽ ፋሲል የኔአለም፣ 16ኛ ተከሳሽ አበበ በለው እና 22ኛ ተከሳሽ ኦባንግ ሜቶ በቀረበባቸው ማስረጃ መሠረት ሊከላከሉ ይገባል ብሏል፡፡
ነገር ግን 12ኛ ተከሳሽ ኤፍሬም ማዴቦ 17ኛ ተከሳሽ አበበ ገላው፣ 18ኛ ተከሳሽ ንአምን ዘለቀ፣ 19ኛ ተከሳሽ ኤልያስ ሞላና፣ 20ኛ ተከሳሽ ደሳለኝ አራጌ እና፣ 21ኛ ተከሳሽ ኮ/ል አለሁበል አማረ አቃቤ ሕግ ከጥርጣሬ በዘለለ በቂ ማስረጃ ሊያቀርብ ባለመቻሉ ነፃ ናቸው በማለት በንባብ አሰምቷል፡፡
በ2ተኛው ክስ የቀረበባቸው ከ1ኛ እስከ 18 ተራ ቁጥር ያሉ ተከሳሾች ላይ ብቻ ነው ያለው ፍርድ ቤቱ፣ ከ 1 እስከ 5 ያሉትና 12ተኛ እና 21ኛ ተከሳሾች በቂ ማስረጃ ስላልቀረበባቸው ፍርድ ቤቱ ከዚህ ክስ ነፃ እንዳደረጋቸው ገልፆ የተቀሩት ግን መከላከል ይገባቸዋል ብሏል፡፡
4ተኛው ክስ ልክ እንደ 1ኛው ክስ ሁሉ በሁሉም ላይ የቀረበ መሆኑን የገለጸው ፍርድ ቤቱ፣ ከ12ተኛ፣ 19ነኛ፣ 20ኛ እና 21ኛ በስተቀር መከላከል ይገባቸዋል፤ ነገር በ5ተኛ ክስ ላይ በሁሉም ተከሳሾች ላይ የሰው፣ የሰነድ፣ የድምጽና የምስል የተባሉት ማስረጃዎች የስለላ ወንጀል ፈጽመዋል ለማለት የሚያስችል መረጃ ባለመቅረቡ መከላከል ሳይስፈልጋቸው ነፃ ናቸው በማለት ገልፆል፡፡
ለአለፉት አምስት ወራት በኢህአዴግ መንግሥት በእስር ላይ የሚገኘው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አንዷለም አራጌ ”ከታሰርንበት ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ በደሎችና ሰቆቃ በመንግስት ቢደርስብንም ይሄ ፍርድ ቤት አቤቱታችንን ሰምቶ የሚደርስብንን በደል ሊያስቆምልን አልቻለም፤ እውነት ፍርድ ቤቱ ለኢትዮጵያ ህዝብና ለፍትህ የሚሰራ ከሆነ የተፈጸመብንን በደል አይቶ እርምጃ ሊወስድ በተገባ ነበር፡፡ ነገር ግን ከፍርድ ቤት በፊት ከጠቅላይ ሚንስትር መለስ ጀምሮ ፍርድ ከቤተመንግሥት በግለሰቦች ሲሰጥ ማየታችን አያስገርመንም በደንብ የታወቀ ጉዳይ ሆኗልና፡፡ ለዚህም ነው ክሱ ከመመስረቱ በፊት አቶ መለስ በኢቲቪ ፍርድ ሰጥተው ያወሩትን ነው ፍርድ ቤቱ እየደገመው ያለው፣ ኢቲቪው እየሰራው ያለው ፕሮፓጋንዳ ይሄንኑ ነው‘ ብሎ ሲናገር ዳኞቹ በተግሳጽ አስቁመውታል፡፡
5ተኛ ተከሳሽ ክንፈሚካኤል ደበበ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አለኝ ብሎ በመነሳት “የኤርትራ መንግስት ተላላኪ የሚል ክስ ቢቀርብብኝም ፍርድ ቤቱ በማስረጃ ተደግፎ ባለመቅረቡ ውድቅ አድርጎታል ፣ ነገር ግን የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በትላንትናው እለትም ከአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር አያይዞ እያቀረበኝ በሀሰት እየወነጀለኝና ሥሜን እያጠፋው ነው” ብሏል፡፡
ፍርድ ቤቱ “አቶ አንዷለም አራጌንና አቶ ክንፈሚካኤል ደበበን ችሎት እየተጋፋችሁና በምትናገሩት ንግግር ዘወትር የፍርድ ቤቱን ልዕልና እየጣሳችሁ በመሆኑ ከዚህ በኋላ ሊያስቀጣችሁ የሚችል መሆኑን እንድታውቁ በማለት ይሄ ፍርድ ቤቱ በአቀረባችሁት አቤቱታ ላይ ሁሉ ትዕዛዝ አስተላልፏል ፣ ነገር ግን ይሄ ችሎት የእናንተን ጉዳይ አየ ማለት ለበደላችሁ ሁሉ ይመለከተዋል ማለት አይደለም ሁሉም ነገር አግባብና የአሰራር ደንብ አለው” በማለት ገልፆል፡፡
ፍርድ ቤቱ የተከሳሽ ምስክሮችን ለማድመጥና የሰነድ ማስረጃዎችን ለመመልከት ለየካቲት 26 እና 27 ቀን 2004 ዓ.ም ቀጠሮ ይዟል፡፡ በችሎቱ ማብቂያ ላይ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ “እኔ በሀሰት የተወነጀልኩ ሰው ነኝ፣ ከግንቦት 7 ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለኝም፤ ይህን ህዝብ እንዲያውቅልኝ እፈልጋለሁ፡፡ በሀሰት ከተመሰረተብኝ ክስ ነፃና ንጹህ ነኝ” ብሏል::