በአፋር ክልል የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ዋና ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ኡመድ አፋሶ አሊ፤ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው በዋስ መፈታታቸው ተዘገበ

ጥር 16 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በአፋር ክልል የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ  ዋና ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ኡመድ አፋሶ አሊ፤ ከሚኖሩበት አዋሽ ፈንታሌ ወረዳ- አዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ ወደሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው  በ5 ሺህ ብር ዋስ መፈታታቸውን ፍኖተ-ነፃነት ዘገበ። 

 ከድርጅቱ ጽ/ቤት የደረሰውን መረጃ በመጥቀስ ጋዜጣው እንደዘገበው አቶ ኡመድ ከመኖሪያ ቤታቸው ወደፖሊስ ጣቢያ የተወሰዱት ባለፈው ቅዳሜ ነው። 

አቶ ኡመድ፦“ ለምንድነው ያሰራችሁኝ?” በማለት ለወረዳው ፖሊስ አዛዥ ለሻለቃ ኑር አብደላ ጥያቄ አቅርበው፦  “ የአፋር ክልል ርዕስ መስተዳደር የሆኑት አቶ እስማኤል አሊሴሮ ከነቤተሰቦቻቸው ወደ ካናዳ ጠፍተው ሊወጡ ሲሉ ተይዘዋል ብለህ ሰዎችን ሰብስበህ አውርተሃል” የሚል መልስ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል። 

 አቶ ኡመድም በማስከተል ፦”በሐሰት ከምትወነጅሉኝ  ለዚህ አባባሌ ለምን ማስረጃ አላቀረባችሁብኝም” የሚል ጥያቄ ማንሳታቸውን  በመጥቀስ፤ ሆኖም ከሳሾቹና አሳሪዎቹ በቂ መልስ እንዳላገኙ ተናግረዋል፡፡ 

አቶ ኡመድ ከዚህ በፊትም በአፋር ክልል  አባላትን ለማፍራት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ከፍተኛ ዛቻና ማስፈራራት እንደተፈፀመባቸው፤ በተለይም “አፋር ባትሆን እናጠፋሃለን” እያሉ የአካባቢው አመራሮች ያስጠነቅቋቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡ 

“ድርጊቱ እኔንና ሌሎች አባላትን ለማስፈራራት፤ እንዲሁም በአፋር አካባቢ ያሉ ችግሮችን ለህዝብ እዳናሳውቅ ለማፈን የሚደረግ ጥረት እንደሆነ ግልጽ ነው” ያሉት አቶ ኡመድ፤ “ የያዝኩት ዓላማ በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ የህዝብንና የሀገርን ፍላጎት ማራመድ እስከሆነና ወንጀል እስካልሰራሁ ድረስ አልፈራም” ሲሉ ማስፈራራያውና እስሩ በ አቋማቸው ላይ የሚፈጥረው ለውጥ እንደሌለ አረጋግጠዋል። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ ባልታወቀ ሁኔታ ከአካባቢያቸው የተሰወሩት በምዕራብ ጐጃም መራዊ ከተማ ነዋሪ የሆኑት የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ /አንድነት/ አባል  አቶ እያዩ መጣ ስንሻው፤ “ምን አግኝቷቸው ይሆን?”በሚል  ከሦስት ወራት የቤተሰብ ለቅሶና የወዳጅ ዘመድ ሀዘን  በሁዋላ ሰሞኑን  አዲስ አበባ ከሚገኘው የፌዴራል ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ መውጣታቸውን ፍኖት ጨምሮ ዘግቧል ። 

  ባለፈው ጥቅምት 15 ቀን አቶ እያዩ ከቤት አንደወጡ በመቅረታቸውና ስለአጠፋፋቸው ፍንጭ የሚሰጥ ሰው ባለመገኘቱ፤የመሰወራቸው ነገር ለቤተሰቦቻቸው ሀዘን በአካባቢው ነዋሪ  ዘንድ ደግሞ መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ቤተሰቦቻቸው አቶ እያዩን ለማፈላለግ ያደረጉት ጥረትም ተስፋ አስቆራጭ ደረጃ ላይ በመድረሱ በሀዘን ላይ መቆየታቸው ተገልጿል።  

ስለሆነባቸው ነገር ይገልጹ ዘንድ የተጠየቁት አቶ እያዩ፦ “እኔ ህጋዊ ሰው ነኝ በምንም ዓይነት ወንጀል ውስጥ አልገባም፡፡ ይህ ሥርዓት ፍትሐዊ ሥርዓት አይደለም የሚል እምነት ስለአለኝ በአንድነት ፓርቲ ተደራጅቼ ሕጋዊና ሠላማዊ ትግል አደርጋለሁ፡፡ በተደጋጋሚ ብአዴን/የኢህአዴግ/ አባል እንድሆን ተጠይቄ እንቢ ብያለሁ፡፡ በርካታ ብር አምጥተው እንካ ቢሉኝ አልቀበልም አልኳቸው፡፡

ጥቅምት 15 ቀን 2004 ዓ.ም “ዓባይ ዙሪያ ሆቴል” ሻይ ለመጠጣት እንደተቀመጥኩ አንድ ታርጋ ያለውና አንድ ታርጋ የሌለው መኪና መጥተው ቆሙ…” ይላሉ። 

አቶ እያዩ ገለፃቸውን ሲቀጥሉ፦” የፌደራልፖሊስ ልብስና ሲቪል የለበሱ ሰዎች ወደ እኔ መጡ፡፡ አንድ ሲቪል የለበሰ ሰውዬ መጥቶ እያያ- መጣ የምትባለው አንተ አይደለህም? አለኝ፡፡ አይደለሁም እኔ እያዩ መጣ እባላለሁ አልኩት፡፡ “ተነስ” ብሎ አስነሳኝ፡፡ 6 ሆነው በመሸከም ታርጋ የሌለው መኪና ላይ ወረወሩኝ፡፡ ጉዞ እንደጀመርን ከመንገድ ላይ መኮንን ፀጋዬ የተባለ የከተማችንን ነዋሪ ይዘው ጫኑት!! ይዘውን በስማ የሚባል ቀበሌ ጫካ ውስጥ አስገቡን፡፡ እኔን ከመኪና አስወርደውኝ እዚህ ቁጭበል፤ተነስ፤እዚያ ተቀመጥ፤እያሉ ሲጫወቱብኝ ዋሉ፡፡ ድርጊታቸው ጫካ ውስጥ አስገብተው ለመግደል እንደሚፈልግ ሰው ነበር፡፡ ወይም በጫካ ውስጥ ለማምለጥ ሞከረብለው ለመግደል አስበው ይመስለኛል፡፡ በመጨረሻ መኪና ላይ መልሰው ጭነው አዲስ አበባ ፌዴራል ወንጀል ምርመራ አስገቡኝ” ብለዋል። 

በማዕላዊ ወንጀል ምርመራ፦”የግንቦት 7 አባል ነህ፤ሰዎችን እየመለመልክ ወደ ኤርትራ ትልካለህ..አሸባሪ ነህ” በማለት በጫና የታገዘ ምርመራ ሲደረግባቸው መቆየቱን፤ ለ24 ቀናት በጠባብ የጨለማ ቤት ውስጥ ተቆልፎባቸው መሰንበታቸውን፤ ፖሊስ ብቻቸውን ፍርድ ቤት አቅርቦ የ 28 ቀናት ቀጠሮ ይሰጠኝ እያለ ሲያሰቃያቸው መክረሙን ያብራሩት አቶ እያዩ፤ በመጨረሻም ለመሰረቱባቸው ክስ አንድም ማስረጃ ሊያገኙባቸው ባለመቻላቸው ከ ሦስት ወራት ስቃይ በሁዋላ ሰሞኑን እንደለቀቋቸው ተናግረዋል። 

 ከ እስር በለቀቋቸውም ጊዜ ፦” ለ አንድም ሰው ስለሆነው ነገር እና ስለመታሰርህ ካወራህ ዳግም አስገብተን ዕድሜ ልክ እንደምናስርህ እወቅ”በማለት የሆነባቸውን ነገር ፈጽሞ እንዳይተነፍሱ እንዳስጠነቀቋቸው ተናግረዋል። 

“ከእንግዲህ ከአንድነት ፓርቲ ጋር የሚያደርጉትን ትግል ይቀጥላሉ ወይ? ” ተብለው የተጠየቁት አቶ እያዩ፦ “የደረሰብኝ ነገር የበለጠ ጥንካሬንፈጥሮብኛል፡፡ የመንፈስ ጥንካሬን አዳብሮልኛል፡፡ ፓርቲዬም በያዘው የትግል ስትራቴጂ የበለጠ እንድተማመንበት አድርጐኛል፡፡ ስለዚህ ትግሌን ዛሬም እንደትላንትቱ በሕጋዊና ሠላማዊ መንገድ አጠናክሬ እቀጥላለሁ፡፡ ሌላ ምንም አማራጭ የለኝም፡፡” ሲሉ መልስ ሰጥተል፡፡

 በምእራብ ጎጃም ዞን 5 ሰዎች የግንቦት 7 እቡእ አባላት ናቸው ተብለው በደህንነት ሀይሎች ታፍነው ተወስደው መታሰራቸውን ከወራት በፊት መዘገባችን ይታወሳል። 

አራቱ የአካባቢው ነዋሪዎች አሁንም የደረሱበት አልታወቀም፤ ይሁን እንጅ ከወጣት እያዩ ቃለምልልስ ለመረዳት እንደሚቻለው ወጣቶቹ ምናልባትም በማእከላዊ  እስር ቤት ሳይታሰሩ አልቀረም።