ጥር 10 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በጋዜጠኛ ኤልያስ ክፍሌ መዝገብ በተከሰሱት ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች ላይ በዳኛ እንዳሻው አዳነ የተመራው ፍርድ ቤት ባስተላለፈው ውሳኔ ጋዘጠኛ ኤልያስ ክፍሌ በ4 የሽብርተኝነት ክሶች ጥፋተኛ ተብሎአል።
ፍርድ ቤቱ የኢትዮጵያ አንድነት ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚአብሄር፣ የአውራምባ ታይምስ ምክትል ዋና አዘጋጅ የነበረውን ጋዜጠኛ ውብሸት ታየ፣ መምህርትና የፍትህ ጋዜጠኛ አምደኛ የሆነችውን ርእዮት አለሙን እና ሂሩት ክፍሌን በሶስት ክሶች ጥፋተኛ ብሎአቸዋል።
ሂውማን ራይትስ ወች ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ውሳኔ ወዲያውኑ ውድቅ አድርጓል። ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሆን ብሎ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽን መብት የሚያፍን በመሆኑ፣ መንግስት ጉዳዩን በአፋጣኝ ውድቅ አድርጎ ጋዜጠኞችን እንዲፈታ፣ ጋዜጠኞች እስር ቤት እያሉ የደረሰባቸውን አሰቃቂ ድብደባ እንዲያጣራ ጠይቋል።
የድርጅቱ የአፍሪካ ተማራማሪ የሆኑት ላታሺያ ባድር ለኢሳት እንደገለጡት የኢትዮጵያ የጸረ ሽብርተኝነት ህግ ገለልተኛ ዘገባን እና ሰላማዊ ተቃውሞን ለማፈን ተብሎ የተደነገገ በመሆኑ ህጉ ሊቀየር ይገባዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ሂውማን ራይትስ ወች ከአለፉት አራት አመታት ወዲህ በተከታታይ ዘመቻ እንደከፈተበት ገልጦ፣ ተቋሙ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ያለው ልዩነት የርእዮት አለም እንጅ ሌላ አይደለም ብሎአል። ላታሽያ ባድር ግን እንዲህ አይነቱን ክስ አይቀበሉትም
ፍርድ ቤቱ በእስረኞች ላይ ውሳኔ በሚቀጥለው ሳምንት ይሰጣል። በሽብርተኝነት የተከሰሰ ሰው የመጨረሻው የቅጣት መጠን 15 አመት ሲሆን ከፍተኛው ደግሞ ሞት ነው።
በሌላ ዜና ደግሞ በነ አቶ በቀለ ገርባ የክስ መዝገብ በህጋዊ ፓርቲ ሽፋን በኦነግ ውስጥ የቡድን ታጣቂ አባል በመሆን በአሸባሪነት ወንጀል በተከሰሱት የመድረክ አባል የኦፌዴን ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ፣ የኦህኮ ፓርቲ ኃላፊ አቶ ኦልባና ለሊሳ እና ሌሎች ሰባት ተከሳሾች ላይ ዐቃቤ- ህግ 4 ቀሪ ምሥክሮቹን ትናንት ረቡዕ አቀረበ፡፡
ተከሳሾች ለፍርድ ቤቱ እንደተናገሩት ዐቃቤ-ህግ በገንዘብ፣ በጥቅማ- ጥቅም የተገዙ ሰዎችን እና የደህንነት ኃይሎችን ነው ምሥክር አድርጎ ያቀረበው። የፌዴራል ዐቃቤ- ህግ የሰው ምሥክሮቹን አቅርቦ መጨረሱን ለፍርድ ቤቱ ያሳወቀ ሲሆን እስከ ዛሬው ችሎት ድረስ 22 ምስክሮችን አስደምጧል፡፡
አንድ የከፍተኛው ፍርድ ቤት የአስተዳደር ሠራተኛ ለሪፖርተራችን እንደገለጹት መንግሥት ለኦነግ አደረጃጀት ቅርበት አላቸው ያላቸውን ግለሰቦች በጥቅማ- ጥቅም ደልሎ ፣ ታማኝ የፓርቲ አባላትን አስማምቶ፣ እና ደብል ኤጀንት ወይም በሁለት ቢላዋ የሚበሉ የደህንነት ሠራተኞቹን ከሞያሌ፣ ባሌ፣ አርሲ ነገሌ፣ አምቦ እና ነቀምት በማሰባሰብ ናዝሬት አንድ ሆቴል ውስጥ አስቀምጦ በአቃቤ- ህግ የምስክረነት አሰጣጥ አለማምዶ ካቀረባቸው 25 ምልምሎቹ ውስጥ ነው ሃያ ሁለቱ ምስክር ሆነው የቀረቡት።
ከተከሳሾቹ አንዱ ” እኔን በቁጥጥር ሥር ያዋለኝ የደህንነት ሠራተኛ ሚስቴን አግብቶ በቤቴ ውስጥ በመኖር ላይ ይገኛል፣ በምስክርነት የመጡብን ሰዎች በጥቅማ- ጥቅም የተገዙ የኦህዴድ አባላትና የደህንነት ኃይሎች ናቸው የሚል ወረቀት ጽፎ በድብቅ ለታዳሚዎች ” አሰነብቧል፡፡
ፍርድ ቤቱ የቀረቡትን የዐቃቤ-ህግ ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎች አይቶ ተከሳሾች ክሱን ይከላከሉ ወይስ አይከላከሉ የሚለውን ብይን ለመስጠት ለጥር 29 ቀን 2004 ዓ.ም ተለዋጭ ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡