በጋምቤላ ሲካሄድ የሰነበተው ግምገማ አነጋጋሪ ሆኗል ሲል ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ገለጠ

ጥር 7 ቀን 2004 ዓ/ም

ት ዜና:-በጋምቤላ ሲካሄድ በሰነበተው ግምገማ ከሥራ አስፈጻሚው ውሳኔ ውጪ መወሰኑ አነጋጋሪ ሆኗል ሲል ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ  ገለጠ፣ የኢሳት የጋምቤላ ምንጮች ግን ፕሬዚዳንቱም በቅርቡ ከስልጣን ይወርዳሉ ይላሉ።

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ለኢሳት በላከው ዜና የጋምቤላ ሕዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ጋሕአዴን/ ከፌደራል ኢህአዴግ ፅህፈት ቤት በተላኩት አቶ ዘመዴ ዘመድኩንና አቶ አለባቸው ንጉሤ አማካይነት ከታህሳስ 17 ቀን 2004 ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው ድርጅታዊ ግምገማ አጀማመሩ ጥሩ   ሆኖ እያለ ውጤቱ ግን ተበለሽቶአል ብሎአል።

የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ የወሰነው ውሳኔ አወንታዊ የነበረ ቢሆንም፣ ውሳኔው ግን መጨረሻ ላይ ከሙስና ጋር በተያያዘ ተገልብጧል።

ሥራ አስፈጻሚው አቶ ኦሞት ኦባንግ ከፕሬዚዳንትነት መንበራቸውና ከፓርቲው ሊቀመንበርነት፣  አቶ ጓናር የር በተመሳሳይ ከምክትል ፕሬዚዳንትነትና ከፓርቲው ኃላፊነታቸው እንዲነሱ እንዲሁም  ሌሎች የከፋ የሙስናና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች አለባቸው የተባሉት ሁለቱ ሥራ አስፈፃሚዎች ከሀላፊነታቸው እንዲነሱ ወስኖ ነበር።

ይሁን እንጅ  ውሳኔው ተገልብጦ ፕሬዚዳንቱ በኃላፊነታቸው እንዲቆዩ መደረጉ በክልሉ ሌላ ችግር እንዲፈጠር ያደርጋል።

የጋራ ንቅናቄው ዘገባ አክሎም  አስገምጋሚዎቹን ለመደለልና ፕሬዚዳንቱን ለመከላከል በክልሉ ሰፋፊ መሬት ያላቸው ባለሃብቶችና ነጋዴዎች ስብሰባ በማካሄድ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አሰባስበዋል።

ባለሃብቶቹንና ነጋዴዎቹን በማስተባበርና መዋጮውን በማሰባሰብ ሥራ ላይ ከማዕከል ፕሬዚዳንቱን እንዲያማክሩ የተላኩት አቶ ብሌን ከፍተኛውን ሚና ተጫውተዋል።

 

ሙሉ በሙሉ በጥፋተኛነት ተፈርጀው እስር እንደሚጠብቃቸው የተገለጸላቸው አቶ ኦሞት ኦባንግ የፕሬዚዳንትነት መንበራቸውን እንደያዙ እንዲቀጥሉ ይፋ ሲደረግ ከወረዳ የመጡ የበታች አመራሮችን ጨምሮ በመሰብሰቢያ አዳራሹ ውስጥ ከፍተኛ ተቃውሞ ተሰንዝሮ ነበር።

በግምገማው የተሳተፉ የፓርቲው አባላት በወቅቱ ስለነበረው ተቃውሞ ያስረዱን “ሰው የማይወደው፣ የሥራ አፈጻጸም ችግር ያለበት፣ ለሰላምና ለጸጥታ ችግር የሆነ፣ በሙስና የተጠመቀ፣ በተለያዩ ወንጀሎች የሚጠየቅ ሰው በኃላፊነት ማስቀጠል አግባብ አይደለም። ችግርም ያስከትላል . . .” በሚል በእልህ የሚናገሩ ነበሩ።

ይሁን እንጂ አቶ ኦሞትን በኃላፊነት ለማስቀጠል አስቀድሞ የተወሰነ ስለነበር  የተሰጠው ምላሽ ማስፈራሪያና ማሸማቀቂያ ብሎአል።

የኢሳት የጋምቤላ ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ ግን ፕሬዚዳንቱ እንደ ምክትሉ ሁሉ መባረራቸው አይቀርም። ፕሬዚዳንቱ “እኔ የምታሰር ከሆነ መለስም መታሰር አለበት” ብሎ መናገሩ አቶ መለስን ቢያስቆጣም ፣ በአሁኑ ጊዜ እርምጃ መውሰድ ነገሩን ማባባስና አላስፈላጊ የሆነ ሌላ መዘዝ መፍጠር ነው በሚል ለጊዜው ታልፈዋል።

ግምገማው በሚካሄድበት ጊዜ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ከስልጣን መባረራቸው እንደተሰማ፣ ኑዌሮች በሚኖሩበት ኒው ላንድ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ከፍተኛ ውጥረት ነበር።

በክልሉ የሚገኘው የግብርና ኮሌጅ ለአንድ ቀን ተዘግቶ እንደነበር፣ የጸጥታ ሀይሎች በአካባቢው በብዛት ተሰማርተው ቅኝት ማድረጋቸውን ፣ ህዝቡም ላለፉት አራት ቀናት ግጭት ይነሳል በሚል ስጋት ውስጥ ግብቶ እንደነበር ፣ ይሁን እንጅ በምክትል ፕሬዚዳንቱ ቦታ የኑዌር ተወላጅ የሆኑት የጸረ ሙስና ኮሚሽነር የነበሩት አቶ ፓትልዋክ ቱት በመተካታቸው መረጋጋት መፈጠሩን ምንጫችን ገልጧል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የሆኑት አቶ ኡሞድ ኡቦንግ ከድርጅት ሀላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጉ እርሳቸውን ለማስወገድ የመጀመሪያው ደረጃ መሆኑ ታውቋል።

ፕሬዚዳንቱ በአቶ መለስ ላይ የሰጡት አስተያየት ግለሰቡ ምናልባትም መጨረሻቸው ስልጣን በመልቀቅ ብቻ ላይቋጭ ይችላል ሲሉ የኢሳት ምንጮች አስተያየታቸውን አስቀምጠዋል።