ጥር 7 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የአወልያ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችና እና የአወልያ ኮሌጅ ተማሪዎች ላለፉት ተከታታይ ሳምንታት ትምህርታቸውን አቋርጠው የተለያዩ ሀይማኖታዊ መብቶችን ሲጠይቁ ነበር።
ተማሪዎች መንግስት አንዳንድ ጥያቄያቸውን በመመለሱ እና ቀሪዎችን ጥያቄዎቻቸውን በመረጡዋቸው ወኪሎች አማካኝነት ለመጠየቅ በመስማማት በዛሬው እለት ትምህርት ጀምረዋል።
ተማሪዎቹ ለኢሳት እንደገለጡት ምንም እንኳ አብዛኞቹ ጥያቄዎቻቸው፣ በተለይም መጅሊስ እንዲፈርስና አህባሽን ያማስፋፋት ተልእኮው እንዲቋረጥ ያቀረቡት ጥያቄ ባይመለስም ፣ አስተማሪዎቻቸው ወደ ስራ ገበታቸው እንዲመለሱ ተደርጓል።
ቀሪዎችን ጥያቄዎች በወኪሎቻቸው አማካኝነት ለመግፋት መወሰናቸውን እና ወኪሎቻቸው ጥያቄዎች አልተመለሱልንም ብለው ለወከላቸው ተማሪዎች ሪፖርት ካቀረቡ አመጹ እንደገና ይጀመራል በማለት ተማሪዎች ተናግረዋል።
የአወልያ ኮሌጅ ግን አሁንም እንደተዘጋ ነው።
ከትናንት ጀምሮ ደግሞ በኤስ ኤም ኤስ፣ በፌስ ቡክ እንዲሁም በስልክ የአዲስ አበባ ነዋሪ ሙስሊሞች በሚቀጥለው አርብ በአወሊያ መስጊድ ተገኝተው ተቃውሞአቸውን እንዲያሰሙ መልእክቶች እየተላለፉ ነው።