ጥር 4 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የአርብ ወይም የጁማን ስገደት ለመስገድ በአወልያ መስጂድ የተገኙት የአዲስ አበባ ነዋሪ ሙስሊሞች፣ ከተማሪዎች ጋር በመሆን የተቃውሞ መፈክሮችን አሰምተዋል።
በርካታ ሙስሊሞች በአወልያ መስጂድ ተገኝተው ስግደት መስገዳቸውን፣ ከስግደቱ በሁዋላ በአንድ ተማሪ አማካኝነት የቀረበውን መፈክር አብረው መድገማቸውን ተማሪዎች ለኢሳት ገልጠዋል።
ከመፈክሮቹ መካከል ምርጫ በነጻነት ይካሄድ፣ መጂሊሱ ይፍረስ፣ የሀይማኖት ነጻነት ይከበር የሚሉ ይገኝበታል።
ለስግደት የሄዱት ሙስሊሞች ተማሪዎችን ሲያበረታቱ ታይተዋል።
የጸጥታ ሀይሎች ሲቪል የለበሱ የደህንነት አባሎቻቸውን ወደ ውስጥ በማስገባት ለመቆጣጠር ቢሞክሩም ሳይችሉ ቀርተዋል። ዛሬ፣ ጥር 4፣ 2004 ከሰአት በሁዋላ ደግሞ ተማሪዎች ስብሰባ አካሂደው በሚቀጥለው ጊዜ ስለሚወስዱት እርምጃ ተወያይተዋል። ተማሪዎቹ ጥያቄያቸው እስከሚመለስ ድረስ አድማውን እንደሚቀጥሉ ይናጋረሉ።
ተማሪዎች ከግቢ ለመውጣት እና ወደ ግቢ ለመግባት እንደማይችሉ አካባቢው በፌደራል ፖሊስ አባላት መከበቡን ይገልጣሉ።
ኢሳት ቀደም ብሎ እንደዘገበው ተማሪዎች መንግስት አህባሽ እየተባለ የሚጠራውን የእስልምና አስተምህሮ መደገፉን አጥብቀው ይቃወማሉ። አንዳንድ በእምነታቸው የተነሳ ከስራ የተባረሩ መምህሮቻቸው እንዲመለሱም ተማሪዎች ጥያቄ ያቀርባሉ።