ጥር 4 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በወረዳው ፈቃድ በህብረተሰቡ የተገነቡ ከ500 መቶ መኖሪያ ቤቶች በላይ በቅርቡ በክልሉ መንግስት ጨረቃ ቤት ተብለው ማክሰኞ እለት በግብረ ኃይል ሊያፈርሱ የተንቀሳቀሱት የወረዳው የጥቃቅን እና እንዱስትሪ ዋና ኃላፊ አቶ ይበሉ ደሴ፣ ምክትል ኃላፊው አቶ እንድሪስ ክንዴ፣ የቤቶች ቁጥጥር ኃላፊው አቶ ገበያው ደምለው እና ፖሊስ ይልማ ተፈራ በታጣቂ ኃይል ይዘውት የመጡትን መሳሪያ ተቀምተው መመታታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
የወረዳው ኃላፊ አቶ ይበሉ ደሴ ህይወታቸው ሲያልፍ ፣ ሌሎቹ ቁስለኞች ደግሞ ባህርዳር ከተማ ፈለገ ህይወት ሆስፒታል የሕክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ነው፡፡ ከህዝቡ ወገን የቆሰሉት ደግሞ ሞጣ ሆስፒታል ገብተው በመታከም ላይ ናቸው።
በአሁኑ ጊዜ ወረዳዋ በፌዴራል ፖሊስ ቁጥጥር ሥር መሆኗን እና በርካታ ሰዎች እየታፈሱ በመታሰር ላይ መሆናቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል። በባለስልጣኖቹ ላይ ግድያውን የፈጸሙት ወጣቶች ከአካባቢው የተሰወሩ ሲሆን፣ እነርሱን ለመያዝ ከፍተኛ የፖሊስ ሀይል በአካባቢው ተሰማርቷል። ወጣቶቹ መሳሪያ ነጥቀው በመጥፋታቸው በአካባቢው ያሉ ባለስልጣናት በስጋት ውስጥ መግባታቸውን የደረሰን መረጃ ያመልክታል።