ጥር 3 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-እንደ ፎርቹን ዘገባ፤መከላከያ ሚኒስቴር በትግራይ-መቀሌ ውስጥ በ165 ሚሊዮን ብር ወጪ ለከፍተኛ የጦር መኮንኖች መዝናኛ የሚሆን ባለ ሦስት ኮከብ ልዩ ሆቴል ለማስገንባት እንቅስቃሴ የጀመረ ሲሆን፤ ሆቴሉን በበላይነት ከመቆጣጠር ባሻገር የንግድ ስራውን የሚያካሂደውም ራሱ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ነው።
በኢትዮጵያ የመከላከያ ታሪክ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ፤ ንግድ ለማካሄድ ሆቴል ሲያስገነባ ፤ይህ የመጀመሪያው ነው።
በመከላከያ ሚኒስቴር አማካይነት መቀሌ ውስጥ በ 1 ሺህ 200 ስኩየር ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ይገነባል የተባለው ይህ ባለ ሶስት ኮከብ ሆቴል፤ ስድስት የተዋቡ ሰፋፊ አዳራሾች እንደሚኖሩት “ ስለሽ” በተባለ አማካሪ ድርጅት የተሠራው ዲዛይን ያመለክታል።
የሆቴል ግንባታውን የሚያካሂደውም፤ የመከላከያ የግንባታና የምህንድስና ኢንተርፕራይዝ መሆኑ ታውቋል።
የግንባታ ስራው በቀጣዮቹ ጥቂት ወራት እንደሚጀመር የገለጹት የመከላከያ ምንጮች፤ሚኒስቴሩ በቀጣይም በአዋሳ፣በባህር ዳርና በአዲስ አበባ ተመሣሳይ ሆቴሎችን አስገንብቶ ለመነገድ ማቀዱን ገልጸዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለተያዘው በጀት ዓመት ከተመደበለት 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ውስጥ፤600 ሚሊዮን ብሩን ለሆቴል ግንባታ እንደመደበ የፎርቹን ዘገባ ያመለክታል።
ከሚገነቡት ከነዚህ ሆቴሎች ውስት ሦስቱ ባለ ሦስት ኮከብ፤በአዲስ አበባ የሚገነባው ደግሞ ባለ አራት ኮከብ እንደሚሆን ዲዛይኖቹ ያሳያሉ።
በአዲስ አበባ በተለየ መልኩ ለመከላከያ ከፍተኛ መኮንኖች መዝናኛ ተብሎ ልደታ በሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፊት ለፊት በ 1000 ስኩየር ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚገነባው ይህ ልዩ ሆቴል ፤60 የተዋቡና ራሳቸውን የቻሉ የመኝታ ክፍሎችን ጨምሮ፤የገልፍ መጫዎቻ፣መዋኛ፣የስብሰባ አዳራሾችና ሌሎች ልዩ ልዩ መዝናኛዎችን ያካትታል።
በመቀሌ የህወሀት ከፍተኛ ሹመኞች ብቻ የሚኖሩበት “አፓርታይድ መንደር” እንደተገነባ በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል።
አብዛኛው የኢትዮጵያ ወታደር ትርጉም በሌላቸው ጦርነቶች እንዲማገድ እየተደረገ ባለበትና ፖሊሶች በደመወዛቸው ከወር እስከ ወር መዝለቅ ባልቻሉበት ወቅት፤ የአቶ መለስ መንግስት ለጀነራሎቹና ለከፍተኛ መኮንኖቹ ምቾት ተጨንቆ በየ ጊዜው በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ማፍሰሱ፤ በሰራዊቱ ውስጥ ቁጣ መቀስቀስ ከጀመረ መሰንበቱን ምንጮች ይናገራሉ።
ሌላው ቀርቶ ወደ ስራቸው ለመምጣት የ አውቶቡስ መሳፈሪያ ያጠራቸው በቃሊቲ እስር ቤት ቤት የሚሠሩ በርካታ ፖሊሶች፤ በየጊዜው ከእስረኞች የሚተራርፍን ዳቦና እንጀራ በፌስታል በማድረግ ለልጆቻቸው ሲወስዱ ይስተዋላሉ።
ለከፍተኛ መኮንኖችና ለጀነራሎች ምቾት እየተባለ በየጊዜው የሚወጣው ገንዘብ ለተራው ወታደርና ፖሊስ ደመወዝ ጭማሪ ቢውል ኑሮ፤በተወሰነም ደረጃ ቢሆን ኑሯቸውን ለመደገፍ ያስችላቸው እንደነበር ፖሊሶቹ በምሬትና በብሶት ሲናገሩ ይደመጣሉ።
እንዲሁም፤እንደ ኢሳት ምንጮች መረጃ፦በርካታ የሰራዊቱ አባላት፦” እኛ ቃለ-ምህላ የፈጸምነው አገርና፣ህዝብን ለመጠበቅ እንጂ፤ የነ አቶ መለስን ስልጣንና የአዛዦቻችንን ምቾት ለመጠበቅ አይደለም” እያሉ በማጉረምረም ላይ ናቸው።
ቀደም ሲል የዚህ ዓይነት ተቃውሞ የሚያሰሙ የሠራዊቱ አባላት በተለያዩ ዘዴዎች ሲታሰሩና ሲባረሩ መቆየታቸውን ያወሱት ምንጮቹ፤ በአሁኑ ጊዜ ግን ቅሬታውና ተቃውሞው በአብዛኛው ዘንድ እየተስተጋባ በመሆኑ ለይቶ ለመምታት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል ብለዋል።
በደርግ መንግስት ውድቀት ዋዜማ አብዛኞቹ የጦር ጀነራሎች፤ ህገ-ወጥ ንግድ ውስጥ መግባታቸውና ምቾታቸውን ወደማስጠበቅ ብቻ ማዘንበላቸው በስፋት ይነገራል።