(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 20/2011)ግንቦት 20 ከትግራይ ክልል በቀር በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች አለመከበሩ ታወቀ።
ከ28 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓሉ ሳይከበር መቅረቱን የተለያዩ የዜና አውታሮች ዘግበዋል።
በትግራይ አክሱም በተከበረው የግንቦት 20 በዓል የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካዔል በግንቦት 20 የተገኘው ድል ባለፉት አራት ዓመታት እየተሸረሸረ መጥቷል ሲሉ መግለጻቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ግንቦት 20ን አስመልክተው ያለፈ ቁስላችንን እየነካካን የነገውን ቀን እንዳናበላሽ የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።
ለወትሮው ግንቦት 20 ሲደርስ የግንቦት ወርን መግባት ተከትሎ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን በህወሃት የትግል ታሪክ ላይ ያተኮሩ ዝግጅቶችን፣ የታጋዮችን ገድልና ትርክት በማቅረብ በዓሉን ያደምቁታል። በዕለቱም በየከተሞቹ ባሸበረቀ መልኩ በዓሉ ይከበራል።
ስብሰባዎች፣ የሻማ ማብራት ዝግጅቶች፡ ግንቦት 20ን የተመለከቱ የተለያዩ ትዕይንቶች የሚደምቁበት ዕለት ነው።
ላለፉት 28 ዓመታት ግንቦት 20 በአራቱም የኢትዮጵያ አቅጣጫዎች ሲከበር ቆይቷል።
ዘንድሮ ከትግራይ ክልል በቀር በዓሉ አለመከበሩ እያነጋገረ ነው።
ዕለቱ የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦች ነጻ ያወጣ፣ ጭቆናን ያስቆመ የሚል መገለጫ ቢሰጠውም ከትግራይ ክልል ውጭ ያለምንም ዝግጅት በዝምታ መታለፉን ነው ኢሳት ወደተለያዩ ከተሞች በመደወል ከነዋሪዎች ያረጋገጠው።
ዕለቱን አስመልክተው ዘገባ ያቀረቡ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃንም ከትግራዩ በዓል ውጪ በሌሎች አካባቢዎች ምንም ዕይነት እንቅስቃሴ አለመኖሩን ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።
በትግራይ በተለያዩ ከተሞች ግንቦት 20 በድምቀት መከበሩ የታወቀ ሲሆን በዋናነትም በአክሱም በልዩ ስነስርዓት እንደተከበረ ተገልጿል።
በአክሱሙ ክብረበዓል ላይ በሰርገላ ሆነው በህዝብ ፊት የቀረቡት የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ደብርጺዮን ገብረሚካዔል የግንቦት 20 ትሩፋቶች ከአራት ዓመት ወዲህ እየተበላሹ መጥተዋል ሲሉ ገልጸዋል።
ዕለቱን አስመልክቶ ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ህወሀት ባወጣው መግለጫ በደርግ ዘመን ከዓለማችን 10 ደሀ ሀገራት አንዷ የነበረችው ኢትዮጵያ በግንቦት 20 በተገኘው ድል ምክንያት ከዓለም በፈጣን ዕድገት ከሚጠቀሱ 10 ሀገራት አንዷ ልትሆን ችላለች ብሏል።
ዶክተር ደብረጺዮን ግንቦት 20 ያስገኛቸው ድሎች አሁን እየተሸረሸሩ መጥተዋል፡ ፌደራል ስርዓቱ በግንቦት 20 የመጣ ስኬት ቢሆንም ያንን ለማጫናገፍ የተለያዩ ሃይሎች ተስልፈዋል ሲሉ ንግግር አድርገዋል።
በመቀሌና በሌሎች የትግራይ ከተሞችም በተለያዩ ስነስርዓቶች መከበሩ ታውቋል።
ግንቦት 20ን አስመልክተው መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ያለፈ በደልና ቁስልን እየነካካን የነገውን ብሩህ ዘመን ማበላሸት የለብንም ብለዋል።
እኔም ቁስል አለኝ ያንተን የሚመስል በሚል መሪ ቃል የተላለፈው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መልዕክት ሁላችንም ተበድለናል፣ ሁላችንም ቆስለናል፡ ዳግም መቋሰል አያስፈልገንም ማለታቸው ተገልጿል።