(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 16/2011)በቅርቡ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ከተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ጋር በተያያዘ ሁለት የመንግስት ሃላፊዎች መታሰራቸው ተገለጸ።
የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በወቅቱ ሁኔታ ላይ መክሮ የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፉን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በቁጥጥር ስር የዋሉት የመተከል ዞን አስተዳደርና ፀጥታ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ፋንቻ አምሳያ እና የግልገል በለስ ከተማ ከንቲባ አቶ ጊሳ ዚፋህ መሆናቸው ታውቋል።
የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ባስተላለፈው አስቸኳይ ውሳኔ መሰረት ግጭት በተከሰተባቸውም ሆነ በየትኛውም የክልሉ አካባቢ ድምፅ አልባ መሣሪያዎችን ይዞ መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡
በግጭቶቹ የተፈናቀሉትን ዜጎች ወደ ቀያቸው ለመመለስ የክልሉ መንግስት ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቋል።
በቤንሻንጉል ጉምዝ መተከል ዞንና በአማራ ክልል ጃዊ ወረዳ በተከሰቱ ግጭቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች ተገድለዋል። በርካቶች ተፈናቅለዋል።
የሁለቱ ክልል መንግስታት ከፌደራሉ መንግስት ጋር በመሆን የበለጠ አደጋ እንዳይከሰት በማድረጋቸው ግጭቶቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ነው የተገለጸው።
የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መንግስት የጸጥታ ምክር ቤት ትላንት ባስተላለፈው ውሳኔ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ በሆኑ አካባቢዎች የጦር መሳሪያ ዝውውርን ጨምሮ የተለያዩ ገደቦችን መጣሉን የደረስን መረጃ ያመለክታል።
ምክር ቤቱ በመተከል ዞን በዳንጉር፣ በማንዱራ፣ በፓዌና በድባጢ ወረዳዎች ተከስተው በነበሩ ግጭቶች መሠረታዊ መነሻ ምክንያቶች ፣ ግጭቶቹን ለማስቆም በተወሰዱ የመፍትሄ ርምጃዎች ፣ እንዲሁም በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ በጥልቀት ተወያይቶ ባስተላለፈው በዚሁ አስቸኳይ ውሳኔ በተደራጀ መንገድም ሆነ በተናጠል ወደ አማራ ክልል አዋሳኞች ጥቃት ለመፈፀም የሚደረጉ ማናቸውም ዓይነት እንቅስቃሴዎች ፍፁም ህገ-ወጥ ፣ በየትኛውም አካላ ተቀባይነት የሌለውና የተወገዘ ከመሆኑም ባለፈ በልዩ ሁኔታ በህግ የሚያስጠይቅ ተግባር ነው ሲል አስቀምጦታል።
የክልሉ የጸጥታው ምክር ቤት ግጭት በተከሰተባቸውም ሆነ በየትኛውም የክልሉ አካባቢ ድምፅ አልባ መሣሪያዎችን ይዞ መንቀሳቀስን በጥብቅ ከልክሏል።
በልዩ ሁኔታ ከተፈቀደላቸው አካላት ውጭ የክልሉ ሚሊሻ አባላትም ሆኑ የቀበሌ ታጣቂዎች ህጋዊም ሆነ ህገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ ነው ሲል አስታውቋል።
ከመከላከያ ሠራዊትና ከፌዴራል ፖሊስ ውጭ በአስተዳደር ወሰን አካባቢዎች የክልሉ ልዩ ኃይል እና መደበኛ ፖሊስ በ5 ኪሎ ሜትር ራዲዬስ ውስጥ መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስ አይቻልም ብሏል ምክር ቤቱ።
ከዚሁ ጎን ለጎን የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥና በግጭቱ ውስጥ የተሳተፉ አካላትን ለህግ ለማቅረብ የተጀመረውን ጥረት ስኬታማ ለማድረግ ያልተቆጠበ ድጋፍ እንዲያደርግ የክልሉ የጸጥታ ምክር ቤት ጥሪ አድርጓል፡፡
በተያያዘ ዜና የመከላከያ ሰራዊት ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመሆን ሁለት የመንግስት ሃላፊዎችን በቁጥጥሩ ስር ማድረጉ ተገልጿል።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከተፈጠረው የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ናቸው ለእስር የተዳረጉት።
እነዚህ ሃላፊዎች የመተከል ዞን አስተዳደርና ፀጥታ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ፋንቻ አምሳያ እና የግልገል በለስ ከተማ ከንቲባ አቶ ጊሳ ዚፋህ መሆናቸው ተገልጿል።