(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 6/2011)በቴፒ የአንድ የሐረማያ ዩንቨርሲቲ ተማሪ በጸጥታ ሐይሎች በመገደሉ ውጥረት መንገሱ ተነገረ።
ልጃቸውን ለመዳር የተዘጋጀው የሟች ቤተሰብ ደስታ ወደ ሀዘን ተቀይሯል ።
በከተማው ሌሎች ሁለት ወጣቶች በጥይት ተመተው በቴፒ ሆስፒታል በመታከም ላይ ይገኛሉ ።
ውጥረቱን ተከትሎ በርካታ የንግድ ተቋማት ተዘግተዋል፣ የትራንስፖርትም አገልግሎት ተቋርጧል።
በቴፒና አካባቢዋ በመከላከያ የሚመራ የኮማንድ ፖስት ቢታወጅም አሁንም ሰላምን ማስጠበቅ እንዳልተቻለ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
በቴፒና አካባቢው በተደጋጋሚን የጸጥታ ችግር በመፈጠሩ በመከላከያ የሚመራ ኮማንድ ፖስት ቁጥጥር እያደረገ ይገኛል።
በዚህ መካከል ግን በቴፒ የአስተዳደር በደል ፈጽመዋል የተባሉ አመራሮችና በሕግ የሚፈለጉ በወንጀል ተጠራጣሪ ግለሰቦች አሁንም አለመያዛቸው ይነገራል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የእህቱን ሰርግ ለመታደም የመጣ አንድ የሃሮማያ ዩኒቨርስቲ ተማሪ በጸጥታ ሃይሎች ተገድሏል።
የአካባቢው ምንጮች ለኢሳት እንደገለጹት ወንዴ መኩሪያ የተባለው የዩኒቨርስቲ ተማሪ በመገደሉ በቴፒና አካባቢው ውጥረት ነግሷል።
ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገው የኢሳት ምንጭ እንደገለጸው ሕዝቡ ወንጀለኞች ለህግ እንዲቀርቡ ቢፈልግም በየኪ ወረዳ በጌጫና በማሻ ግጭት እንዲፈጠር ያደረጉ የአካባቢው አመራሮች እንዲያዙ ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ አላገኘም።
መከላከያ በሕዝቡ ላይ ብቻ አነጣጥሮ በወጣቱ ላይ ግድያ መፈጸሙ ትክክል አይደለም ብሏል የቴፒና የአካባቢው ነዋሪ።
እናም ሕዝቡ በመማረሩና ችግሩን የሚፈታለት ባለማግኘቱ የንግድ መደብሮች ተዘግተው ትራንስፖርት እንዲቋረጥ መደረጉን ገልጿል።
ወቅቱ የእርሻ ስራ ወቅት ቢሆንም የቴፒና አካባቢው ሕዝብ ለሰላም ባለመታደሉ የመንግስት ያለህ እያለ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።