(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 28/2011) የብፁዕ ዶክተር አቡነ ገሪማ የቀብር ስነስርዓት የፊታችን እሁድ እንደሚፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስ አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በተለያዩ ሃላፊነቶችና ሃይማኖታዊ ተልዕኮዎች ሲያገለግሉ የቆዩት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገሪማ ህይወታቸው ያለፈው በትላንትናው እለት ነው።
በእምነቱ ከፍተኛ መለኮታዊ የትምህርት ደረጃ ላይ በመድረስ ከሚጠቀሱ አባቶች አንዱ የሆኑት ዶክተር አቡነ ገሪማ ከ፵ዓመታት በላይ ቤተክርስቲያኒቱን ማገልገላቸውን ለማወቅ ተችሏል።
ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገሪማ እስካለፈው ሰኞ ሚያዝያ 21 ቀን 2011 ድረስ በፓትርያርኩ ልዩ ጽሕፈት ቤት የውጭ ግንኙነት የበላይ ሃላፊነት፣ ሥራቸውን በማከናወን ላይ እንደ ነበሩም ሃራ ዘተዋህዶ ካወጣው መረጃ ላይ ማወቅ ተችሏል፡፡
በሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ ተብለው በኤጲስ ቆጶስነት የተሾሙት ሐምሌ 9 ቀን 1973 ዓ.ም በሰሜን ሱዳን – ካርቱም እንደነበር የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል።
ብፁዕ ዶክተር አቡነ ገሪማ፣ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት፣ ወደ ኋላም የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ኾነውም አገልግለዋል፡፡
በዐበይት በዓላት ላይ በሚያቀርቧቸው፣ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ እና ሐዋርያዊ ተልእኮ ላይ በአተኮሩ ጽሑፋዊ ስብከቶችና ትምህርቶች የሚታወቁት ብጹእ አቡነ ገሪማ ከ30 በላይ የትምህርታዊ ጽሑፎች ስብስብን በ2006 ዓ.ም. ለኅትመት ማብቃታቸውም ይታወቃል፡፡
ብጹእ ዶክተር አቡነ ገሪማ የተወለዱት በሰሜን ሸዋ በ1937 ዓ.ም. ነበር፡፡
ማዕርገ ዲቁናን ከግብፃዊው አቡነ ቄርሎስ፣ ማዕርገ ምንኵስናን መጋቢት 1973 ዓ.ም. በደብረ ሊባኖስ ገዳም እንደተቀበሉም ከሕይወት ታሪካቸው መረዳት ተችሏል፡፡