ጥር 1 ቀን 2004 ዓም
ኢሳት ዜና:-የአፋር ህዝብ ፓርቲ ባወጣው መግለጫ፣ አባቃላ እየተባለ በሚጠራው የማጎሪያ ካምፕ ውስጥ በርካታ የተቃዋሚ መሪ ዘመዶች እና መንግስትን የሚቃወሙ አፋሮች በብዛት እየታጎሩ ነው።
ከ300 በላይ የሚሆኑት አፋሮች ላለፉት 2 አመታት ፍትህ አጥተው በእስር ላይ እንደሚገኙ ፓርቲው አስታውቋል።
የአፋር ህዝብ ፓርቲ ዞን አንድ፣ ዞን ሁለትና ዞን ሶስት እየተባለ በሚጠራው አካባቢዎች አርብቶ አደሮችን እያፈናቀሉ መሆኑን ጠቅሶ፣ ይህን ፖሊሲ የተቃወሙት ሁሉ ከስራቸው እየተባረሩና እየታሰሩ ነው ብሎአል።
የአዋሽ ወንዝን ለተንዳሆ የሸንኮራ እርሻ ተክል በሚል አቅጣጫው እንዲቀየር በመደረጉ ፣ የ ዳትባካሪ የሚገኙ ገበሬዎች በውሀ እጥረት ምክንያት የእርሻ መሬታቸውን እንዲተው ተገዷል ብለዋል። ናማሊፋን በሚባለው አካባቢ የሚገኙ የዶኮ ገበሬዎች የእርሻ መሬታቸውን ለቀሰም የሸንኮራ ተክል አስረክበዋል። አብዛኞቹ ገበሬዎችም ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው በችግር ላይ ይገኛሉ ብሎአል።
የገዢው ፓርቲ ሰዎችም ባቃዱ በተባለው አካባቢ የተለያዩ ጎሳዎችን ለማጋጨት እየሞከሩ ነው ሲል አትቷል።
የአፋር ክልል ፕሬዚዳንት የሆኑት ኢስማኤል አሊሴሮ፣ እንዲሁም የክልሉ ባለስልጣናት የሆኑት ሙሀመድ ከድር እና ስዩም አዋል የክልሉን መሬት ያለህዝብ ፈቃድ ለሶማሊያ ክልል ለመስጠት የሚደረገውን እንቅስቃሴም አውግዟል።
ፓርቲው አያይዞም መንግስት የአፋርን ባህላዊ የአስተዳደር ለማንቋሸሽ ያለውን ፍላጎት በቅርቡ የአውሳ ሱልጣን በሚነግሱበት ጊዜ አሳይቷል ካለ በሁዋላ፣ የአናሳው መንግስት በክልሉ እየፈጸመ ላለው እኩይ ድርጊት ዋጋ ይከፍላል ሲል አስጠንቅቋል።