(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 25/2011)የጎሳ ፖለቲካ በህግ ይታገድ በሚል ዘመቻ በማድረግ ላይ የሚገኙ የተለያዩ ግብረሃይሎች ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ያዘጋጁትን ደብዳቤ አስገቡ።
ግብረሃይሎቹ በአሜሪካን የኢትዮጵያ አምባሳደር በኩል ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብዳቤውን መላካቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ግብረሃይሎች ከአምባሳደር ፍጹም አረጋ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸውም ታውቋል።
ደብዳቤውን ለአምባሳደሩ ካስገቡት መካከል የኢትዮ-አሜሪካ ሲቪል ካውንስል ፕሬዝዳንት ዲያቆን ዮሴፍ ተፈሪ ከኢሳት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት ይህን ዘመቻ ከጀመርን አንድ አመት አልፎናል።
ሲጀመር ጥያቄው ከባድ ቢመስልም በኋላ ላይ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሃሳቡ ተሳታፊ መሆን ችለዋል በዚህም ውጤት ማስመዝገብ ችለናል ነው ያሉት።
እንደ ሃገር ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው ያሉት ዲያቆን ዮሴፍ ይህንን ችግር ለመቅረፍና ሃገርን እንደሃገር ለማስቀጠል የጎሳ ፖለቲካ በህግ መታገድ ይኖርበታል።
ለዚህ ደግሞ ስልጣን ላይ ያለውን አመራር ቁርጠኝነት ይጠይቃል ነው ያሉት።
በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ለሆኑት አቶ ፍጹም አረጋ ደብዳቤያችንን አስገብተናል ያሉት ዲያቆን ዮሴፍ እሳቸውም ደብደቤያችንን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚያደርሱ ቃል ገብተውልናል ብለዋል።