ጥር 1 ቀን 2004 ዓም
ኢሳት ዜና:-በፈረንሳይ መዲና ልዩ ስሙ ካሌ እየተባለ በተለምዶ በሚጠራው ኣካባቢ ኣስገዶም ዮናታን (ኢስማኢል ኢብሳ )የተባለ ኢትዮጵያዊ በፖሊሶች ተደብድቦ መገደሉ ተሰማ ፡፡
ጋዜጠኛ ዘላለም ገብሬ ከአሜሪካ እንደዘገበው “ከፈረንሳይ ወደ እንግሊዝ ለመግባት ጥረት በማድረግ ላይ እያሉ በፈረንሳይ ፖሊሶች እና በኢትዮጵያኖች መካከል በተነሳው ኣለመግባባት አና በተፈጠረው ግብ ግብ መሰረት ህይወቱ አልፎአል።
ወጣት ከደረሰበት ጉዳት ህይወቱን ለመታደግ ወደ ሆስፒታል ቢወሰድም በቂ እርዳታ ሳያገኝ ህይወቱ አልፎአል ፡፡
የወጣቱን ኣስከሬን ለማግኘት 7ሺ ዩሮ ካልከፈላችሁ ልትወስዱት ኣትችሉም በመባሉ፣ የወጣቱ አስከሬን በሆስፒታል የአስከሬን ማቆያ አና ማቀዝቀዣ ውስጥ ተቀምጦ አንደሚገኝ ተጠቁሞኣል፡፡
ፈረንሳይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሟቹ ወጣት የኤርትራ ዜግነት ያለው እንጂ ኢትዪጵያዊ አይደለም ያለ ሲሆን፣ የኤርትራ ኤምባሲ በበኩሉ ወጣቱ ኤርትራዊ ባለመሆኑ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ሊታደገው ይገባል ሲል ምላሹን ሰጥቷል።
በፈረንሳይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ይህ በእንዲህ እንዳለ የሟቹን ኢስማኢል አስከሬን ወደ ሃገር ቤት ለመላክ የአንድ ሳምንት ጊዜ ብቻ ከሆስፒታሉ አስተዳደር አንደተገለጸላቸው ተናግረዋል ።ይህ ካልሆነ ግን የወጣቱ የቀብር ስነ-ስርአት በፈረንሳይ ሊከናወን እንደሚችል አሳውቀዋል ፡፡