(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 15/2011) የሰርሃ ዛላምበሳ ድንበር በቅርቡ ሊከፈት እንደሚችል ተገለጸ።
የኤርትራ መንግስት ባለስልጣናትን ጠቅሶ የኤርትራ ፕሬስ እንደዘገበው ሰሞኑን ከተዘጉትና ኢትዮጵያንና ኤርትራን ከሚያገናኙ ድንበሮች መካከል በዛላምበሳ በኩል ያለው በቅርቡ ይከፈታል።
ኤርትራ የኢትዮጵያን የወደብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ወደ ምጽዋ የሚወስዱ መንገዶችን በመስራትና በመጠገን ላይ መሆኗንም አስታውቃለች።
የድንበሮቹ መዘጋት ከባድ ተሽከርካሪዎችን የሚያስተናገዱ አቅም ያላቸው መንገዶችን ለመስራት ሊሆን እንደሚችልም ተጠቁሟል።
ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያገናኟትን ሁለት ድንበሮች በአንድ ሳምንት ውስጥ መዝጋቷ የሚታወስ ነው።
ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያገኟትን ድንበሮች በሙሉ መዝጋቷን ተከትሎ ጉዳዩ ትኩረትን ስቧል።
ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ የተከፈቱት ድንበሮች በተከታታይ እንዲዘጉ በኤርትራ በኩል የተሰጠ ይፋዊ ምክንያት የለም።
የኢትዮጵያ መንግስትም በጉዳዩ ላይ መግለጫ አልሰጠም።
በሁመራ አቅጣጫ የሚገኘው የኡምናሀጅር ድንበር መዘጋቱ ከሱዳን ጋር ኤርትራ የገባችበትን ፖለቲካዊ ትኩሳት ተከትሎ መሆኑን የኤርትራ መንግስት ባለስልጣናትን በምንጭነት ጠቅሶ ኤርትራ ፕሬስ ዘግቧል።
የዛላምበሳና የቡሬ ድንበሮች የተዘገቡትን ምክንያት በተመለከተም በሁለቱ መንግስታት የተሰጠ ማብራሪያ ባይኖርም ከህገወጥ ንግድ ዝውውር ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ፍንጮች መታየታቸው ታውቋል።
የአፋር ክልል ባለስልጣናት ከቡሬ አሰብ የተዘረጋውና ሁለቱን ሀገራት የሚያገናኘው ድንበር የተዘጋው በዚሁ የህገወጥ የንግድ ዝውውር ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።
ዛሬ በወጣው የኤርትራ ፕሬስ ዘገባ መሰረት ግን የዛላምበሳ ድንበር በቅርቡ ይከፈታል።
የኤርትራዋን ሰርሃ ከኢትዮጵያዋ ዛላምበሳ የሚያገናኘው ድንበር ከተዘጉት ድንበሮች በቅድሚያ ሊከፈት ይችላል በሚል የኤርትራ መንግስት ባለስልጣናትን ጠቅሶ ዘግቧል።
ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በሚያዋስኗት የድንበር አካባቢዎች የሚገኙ መንገዶች በመስራትና በመጠገን ላይ መሆኗን የሚገልጹት የኤርትራ ባለስልጣናት መቀሌ ድረስ የሚዘልቅ ደረጃውን የጠበቀ የአስፋልት መንገድ ለመስራት በዝግጅት ላይ መሆኗን መግለጿን ኤርትራ ፕሬስ ገልጿል።
ወደ ምጽዋ የሚወስደውን መንገድ ምቹ ለማድረግና የኢትዮጵያን የወደብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ታስቦ በተለያዩ ምዕራፎች የሚሰሩ መንገዶች መኖራቸውን የጠቀሰው ዘገባው ለዚህ ትልቅ የመንገድ ስራ የሚያስፈልጉ የበጀትና የዕቃ አቅርቦት ዝግጅት መደረጉን የኤርትራ ምንጮችን በመጥቀስ ኤርትራ ፕሬስ ዘግቧል።
ከባድ ተሽከርካሪዎችን ሊያስተናግዱ የሚችሉ መንገዶችን በመስራት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚረዳ ነው የተገለጸው።
የዛላምበሳው ድንበርም በቅርቡ ይከፈታል ብለዋል ባለስልጣናቱ። በቀጣይም ተሰነይን ከሁመራ የሚያገናኝ የመንገድ መስመር ሊሰራ እንደታቀደም በዘገባው ተመልክቷል።
በሶስቱም አቅጣጫዎች የመንገድና የመሰረተ ልማት ዝርጋታው ተጠናቆ ሁሉም ድንበሮች በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት ከማለቁ በፊት ክፍት እንደሚሆኑ ተገልጿል።