(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 27/2011) የኢትዮጵያ መንግስት የጸጥታና ደህንንት ተቋማትን የአንድ ዓመት ክንውን ይፋ አደረገ።
በአራቱ የጸጥታና የደህንነት ተቋማት ላይ ስር ነቀል ማሻሻያ በመደረግ ላይ መሆኑን አስታውቋል።
በዛሬው ዕለት ለሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የጸጥታና ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ሙሉነህ በማሻሻያው ተቋማቱ ኢትዮጵያዊ ቅርጽ እንዲኖራቸው ማድረግ ትኩረት ተሰጥቶበት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የተልዕኮ ግልጽነት ሳይኖራቸው ህዝብ ላይ አፈናና ሲፈጽሙ የነበሩና በዘረፋ ተግባር የተሰማሩት ብሔራዊ የመረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት እንዲሁም የኢንፎርሜሽን መረብ ኤጀንሲ ሙሉ በሙሉ የአሰራርና የአደረጃጀት ለውጥ እየተደረገባቸው እንደሆነም አማካሪ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ሙሉነህ የቀረበው የአንድ ዓመት ሪፖርት የመከላከያ ሚኒስቴር፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት፣የኢንፎርሜሽን መረብ ኤጀንሲና የፌደራል ፖሊስን ማሻሻያዎች በዝርዝር ያመላከተ ነው።
የሃገሪቱን ጸጥታና ደህንነት በበላይነት የሚቆጣጠሩትና የሚመሩት እነዚህ ተቋማት ትላንት የነበራቸውን ቁመናና ቅርጽ በሚለውጥ መልኩ በማሻሻያው ሰፊ ለውጥ መደረጉን ነው አማካሪ ሚኒስትሩ የገለጹት።
በለውጡ ዋዜማና ማግስት ባሉት ጊዜያት ከ10ሺህ በላይ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ነጻ መደረጋቸው፣ ከፖለቲካና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከሃገራቸው ርቀው የነበሩ ከ70ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት መግባታቸውንም አስታውቀዋል።
በመንግስት በኩል ስርነቀል ማሻሻያ እንዲደረግባቸው ታቅደው ስራቸው እየተከናወነ የሚገኙት የጸጥታና ደህንነት ተቋማት ስማቸው የጎደፈ፣ በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ የሚቀርብባቸው እንደነበሩ የጠቀሱት አማካሪ ሚኒስትሩ አቶ ተመስገን ሙሉነህ በአራት የለውጥ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ማሻሻያ እንደተደረገባቸው በዝርዝር ገልጸዋል።
የአመራር ለውጥ፣ የአመለካከት ለውጥ፣ የአሰራር ስርዓት ለውጥና የአደረጃጀት ለውጥ በተሰኙ አቅጣጫዎች የተደረጉት ማሻሻያዎች ተግባራዊ ተደርገዋል ብለዋል።
ማሻሻያው በዋናነት ተቋማቱ የሚታወቁበትን የአንድ የፖለቲካ ሃይል አለፍ ብሎም የአንድ ብሔር ወገንተኝነትን በሚያስወግድ መልኩ መዋቀሩን የጠቀሱት አማካሪ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያዊ ቅርጽና መልክ እንዲኖራቸው ማድረግ የማሻሻያው ስራ ዋናው መገለጫ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በፊት የነበረው የየተቋማቱ አመራር ከህዝብ ጥያቄ የሚነሳበት፡ ፍትሃዊነት የጎደለው፡ ወደአንድ ፓርቲና ብሔር ያዘነበለ እንደሆነ በሪፖርቱ ተመልክቷል።
ይህንን ማሻሻያው አስተካክሎታል ያሉት አቶ ተመስገን ሙሉነህ የአንድ ብሄር የበላይነት የነበረው አመራር ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል ብለዋል።
ከአመራር ጋር በተያያዘም በርካታ የየተቋማቱ መሪዎች በህግ ጥላ ስር እንዲሆኑ ተደርገው በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በሌብነት በተጠረጠሩባቸው ወንጀሎች ይጠየቃሉ ሲሉ ገልጸዋል።
የአመለካከት ለውጡም የፖለቲካ ወገንተኝነትን በሚያስቀር መልኩ በማሻሻያው የተዘጋጀ ነው ብለዋል።
ከአሰራር ስርዓት ለውጥ አንጻር ዓለም ዓቀፍ ቁመና እንዲኖራቸው በመሰራት ላይ እንደሆነም ተመልክቷል።
ከተልዕኳቸው ውጪ የልማት ድርጅት እስከመሆን ደርሰው በሆቴልና ሪል ስቴት ቢዝነስ ውስጥ የተዘፈቀው የኢንፎርሜሽን መረብ ኤጀንሲ አሰራሩ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ተደርጎ የህዝብን ጸጥታና ደህንነት በማስጠበቅ ተልዕኮ ላይ ብቻ እንዲወሰን ተደርጓል ብለዋል አማካሪ ሚኒስትሩ።
ኤጀንሲው በሁለት ማህተሞች ሲገለገል እንደነበረ፣ ከ8 በላይ የልማት ድርጅቶችን በማስተዳደር ህገወጥ ተግባር ላይ ተሰማርቶ የሀገርን ህልውና አደጋ ላይ ጥሎ መቆየቱን በአንድ አመቱ ሪፖርት ላይ ተመልክቷል።
በጸጥታና ደህንነት ተቋማት ላይ እየተደረገ ያለው ማሻሻያ አዋጆችንም በአዲስ መልክ ይዞ መውጣቱን ነው አቶ ተመስገን የገለጹት።
መከላከያ ሚኒስቴር ከዚህ አንጻር አዳዲስ አዋጆችን በመያዝ ለውጡን እንደሚከተል ተገልጿል።
የእጩ መኮንነት ስልጠና ከወታደራዊ መስመር በተጨማሪ ሲቪሉ የህብረተሰብ ክፍል እንዲገባበት በማድረግ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን የሚያደርግ አዲስ አሰራር ተዘርግቷል ብለዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ካሏት የመከላከያ አደረጃጀቶች በተጨማሪ የባህር ሃይልና የሳይበር ስፔስ ሃይል የተሰኙ ሁለት አዲስ መዋቅሮች እንደተደራጁም ተመልክቷል።