(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 25/2011) በአፋር ገዋኔ አንድ ወጣት በመከላከያ ሃይል መገደሉ ተሰማ።
የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት በመከላከያ ሃይሉ የተገደለው ወጣት ፍየሎችን በመጠበቅ ላይ የነበረ ነው።
የመከላከያ ሃይሉ ጥቃት ሰላማዊ ሰልፍ ሲያደርጉ የነበሩት ወጣቶች ላይ ሊሰነዝር ያሰበውን ጥቃት ነው በዚህ ወጣት ላይ የፈጸመው ይላሉ።
ለሚመለከተው አካል አቤት ብንልም የሚሰማን አካል አላገኘንም ብለዋል።
በገዋኔ የመከላከያ ሃይሉ ፈጸመ የተባለውን ጥቃት አላውቅም ያሉት የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወጣቶቹ ስላነሱት ጉዳይ ግን ከሚመለከተው አካል ምላሽ ተሰቷቸዋል ብለዋል።
በአፋር ክልል ሰሞኑን በክልሉ የተሾመው አዲስ አስተዳደር የሰጠንውን የቤት ስራ መስራት አልቻለም፣ላቀረብንለትም ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ አልሰጠንም በሚል ወጣቶችና የክልሉ ነዋሪዎች ሰልፍ ማካሄዳቸው ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል።
በተለያዩ ወረዳዎች የተካሄደው ሕዝባዊ ሰልፍ አዲሱ አመራር እየሄደበት ያለው ርቀት ትክክል አይደለም።ድሮ ታግለን የጣልንውን አስተዳደር አሰራር እየተገበረ ነው ስለዚህ ሊስተካከል ይገባዋል ሲሉ ነበር ጥያቄያቸውን ያቀረቡት።
የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት እንዳሉት ወጣቶቹ ባካሄዱት ሕዝባዊ ሰልፍ ላይ የመከላከያ ሃይሉ ርምጃ እንዲወስድ ታዞ ነበር።ያ ባይሳካም ዛሬ ግን ተግባራዊ አድርጎታል።
የመከላከያ ሃይሉ በገዋኔ አንድ ወጣትን መግደላቸው በመናገርም ጭምር።
የወጣቱም ሆነ የክልሉ ነዋሪ እያነሳ ያለው ጥያቄ አሁንም አለተመለሰም ይላሉ ነዋሪዎቹ።
የአፋር ክልልን ችግር እንደ ችግር አይቶ ምላሽ የሚሰጥ አንድም አካል የለም ብለዋል።
የአፋር ክልል ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኡስማን ማክበል ዛሬ ገዋኔ ላይ ተገደለ ስለተባለው ወጣትም ሆነ በአካባቢው ስለተፈጠረው ነገር ምንም መረጃ የለኝም ብለዋል ለኢሳት።
ነገር ግን ሰሞኑን ወጣቶቹ ሲያነሱ ለነበረው ጥያቄ ከሚመለከተው አካል ምላሽ ተሰቷቸዋል ነው ያሉት ።
አቶ ኡስማን እንደሚሉት ከሆነ ወጣቶቹ ጥያቄ ማንሳት ይችላሉ የሚመለከተው አካል ደግሞ በዚህ ጉዳይ ላይ ምላሽ መስጠት ግዴታው ነው።*-ከዚህም በመነሳት አጥጋቢ ምላሽ ሰተናል ይላሉ።
እሳቸው ይህን የበሉ እንጂ ጥያቄያችን አልተመለሰልንም ያሉት የክልሉ ነዋሪዎች ጥያቄያቸውን ማቅረብ እንደሚቀጥሉ ለኢሳት ባደረሱት መረጃ አመልክተዋል ።