(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 24/2011)አቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳ ፍርድ ቤት የፈቀደልን የዋስትና መብት ይከበርልን ሲሉ ጠየቁ።
በባህርዳር ከተማ ጉዳያቸው እየታየ የሚገኙት የቀድሞ የኢህ አዴግና የብ አዴን ከፍተኛ አመራሮች ፍርድ ቤቱ በነጻ እንዲያሰናብታቸውም ጠይቀዋል።
በሌብነት ወንጀል የተጠረጠሩት አቶ በረከትና አቶ ታደሰ ባለፈው ሳምንት በፍርድ ቤት የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ውሳኔ መተላለፉ የሚታወስ ነው።
ዛሬ ባህርዳር ላይ ለተሰየመው ችሎች ጥያቄአቸውን ያቀረቡት ተጠርጣሪዎቹ የአማራ ክልል ጸረ ሙስና ኮሚሽን እስካሁን ክስ ስላልመሰረተብን ፍርድ ቤቱ በነጻ እንዲያሰናብታቸው መጠየቃቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በነጻ መሰናበት ካልቻሉም የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል።
አቃቤ ህግ በበኩሉ የምርመራ መዝገቡ ከደረሰኝ በ15 ቀናት ውስጥ ክስ ለመመስረት ጊዜ አለኝ በማለት ተከራክሯል።
ግለሰቦቹ የተጠረጠሩበት የሌብነት ወንጀል ዋስትና የሚያሰጥ አይደለም ሲል የሞገተው አቃቤ ህግ ባለፈው ሳምንት የተፈቀደው የዋስትና መብት ተገቢ አይደለም ብሏል።
በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለመጋቢት 26 ቀጠሮ መሰጠቱን ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።