(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 18/2011) የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ምስረታ ጥረታችን በአመጸኞችና በዕብሪተኞች ድርጊት አይገታም ሲል አርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ባወጣው መግለጫ አመለከተ።
አርበኞች ግንቦት 7 ባወጣው መግለጫ ለረጅም ዓመታት ከታገለላቸዉ መብቶች ዉስጥ አንዱ ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ ባልተስማማበት ሀሳብ፥ፖሊሲና ፕሮግራም ላይ ህግና ደንብን እስካከበረ ድረስ ያለምንም መከልከል በፈለገዉ መን ገድ ተቃዉሞዉን መግለጽ እንዲችል ነዉ ብሏል።
ነገር ግን ዛሬ አገራችን ዉስጥ በግልጽ የሚታየዉ የዜጎች መብትና ነጻነት ሁኔታ በምንም ዓይነት ህገወጥነትንና አመጽን አማራጭ ለማድረግ የሚያሰገድድ ነዉ ብሎ አያምንም።
ባለፈዉ እሁድ መጋቢት15/ 2011ዓ.ም ባህርዳር ዉስጥ አርበኞች ግንቦት 7 ያዘጋጀዉ ህዝባዊ ስብሰባ እንዳይካሄድና ህዝብ ሀሳቡን በነጻነት እንዳይገልጽ መሳሪያ የታጠቁ ኃይሎች የወሰዱት ፍጹም ፀረሰላም የሆነ ርምጃ አገርን ለማረጋጋት በሚደረገዉ ከፍተኛ ጥረት ላይና በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ የረጅም ጊዜ የዴሞክራሲ ጥማቱን ለማርካት በሚያደርገዉ አገራዊ እንቅስቃሴ ላይ ጥቁር ነጥብ ጥሎ ያለፈ ነው ብሏል።
የእሁዱ የባህርዳር ድርጊት በአንድ በኩል የተለያዩ ፀረ ለዉጥና ፀረሰላም ኃይሎች የጋራ ድርጊት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ድርጊቱ በተናጠል፣በአንድ ድርጅት ወይም ግለሰብ ላይ የተወሰደ ርምጃ ሳይሆን ፣ለዘመናት ሲረገጥና ሲገፋ ለኖረዉ የኢትዮጵያ ህዝብ የመጨረሻ እድል በሆነዉ የለዉጥ ሂደት ላይ የተቃጣ አደገኛና ነገ ዛሬ ሳይባል በአፋጣኝ መቆም ያለበት የሁላችንም ፈተና ነዉ ብሎ አርበኞች ግንቦት 7 ከልቡ ያምናል ብሏል።
ስለሆነ ም አርበኞች ግንቦት 7 ይህንን አገራዊ ችግር ከምንም ነገር በላይ አክብዶ አይቶታል ነው ያለው ።
የምርጫ ቦርድና ተፎካካሪ ድርጅቶች፣ባለፈዉ እሁድ ባህርዳር ዉስጥ የታየዉ አደገኛ እንቅስቃሴ እየሰፋ ከሄደ በለዉጡ የተከፈተዉ የፖለቲካ ምህዳር ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ሊዘጋ እንደሚችል ተገንዝባችሁ ድርጊቱን የፈጸሙና እንዲፈጸም ያገዙ ግለሰቦች ለህግ እን ዲቀርቡ ለማድረግ በሚደረገዉ ጥረት ላይ የየራሳችሁን አስተዋጽኦ እንድታደርጉ አርበኞች ግንቦት 7 ወገናዊ ጥሪዉን ያቀርባል ሲል መግለጫው አመልክቷል።
የፌዴራልም ሆነ የክልል የህግ አስከባሪ አካላት ባህርዳር ዉስጥ የተፈጸመዉንና የዜጎችን መብትና ነጻነት የረገጠዉን ድርጊት በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ያቀዱ፣የረዱና በድርጊቱ የተሳተፉ ግለሰቦችን ለህግ አቅርባችሁ አስፈላጊዉን የህግ ርምጃ እንድትወስዱና የወሰዳችሁትን ርምጃ ለመላዉ የሀገራችን ሕዝብ እንድታስታዉቁ አደራ እያልን ፣የዜጎችን መብትና ነጻነት ለማስከበር በምታደርጉት ጥረት ድርጅታችን አስፈላጊዉን ትብብር እንደሚያደርግ ከወዲሁ መግለጽ እንወዳለን ሲል በመግለጫው ጠይቋል ።