(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 25/2011) በፕሬዚዳንት ትራምፕና በሩሲያ መካከል ድብቅ ሴራ ስለመኖሩ መረጃ አለማግኘቱን ጉዳዩን ለማጣራት የተቋቋመው ልዩ ምክር ቤት አስታወቀ።
በሮበርት ሙለር የሚመራው ልዩ ምክር ቤት ጉዳዩን በተመለከተ ላለፉት ሁለት አመታት ሲያደርግ የቆየውን ማጣራት በተመለከተ ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል።
ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዊሊያም ባርም የልዩ ምክር ቤቱን የሁለት አመት የምርመራ ውጤት ለኮንግረሱ አቅርበዋል።
በሮበርት ሙለር የተመራው ልዩ ምክር ቤት የዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ከሩሲያ ጋር በመሆን በ2016ቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጊዜ ሴራ መጠንሰሱን የሚያሳይ ማስረጃ አላገኘሁም ብሏል።
በሪፖርቱ ማጠቃለያም አሜሪካዊ ዜጋ ወይም የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ አስተባባሪዎች በምርጫ ሂደቱ ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር ከሩሲያ ጋር ስለማበራቸው የሚያሳይ ማስረጃ ልዩ ምክር ቤቱ አለማግኘቱን ጠቅሷል።
ይሁን እንጅ አሁን በልዩ ምክር ቤቱ የወጣው ሪፖርት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ነጻ ስለመሆን አለመሆናቸው ግን የገለጸው ነገር የለም።
ውጤቱ ይፋ መሆኑን ተከትሎም ጵሬዝዳንት ትራምፕ በምርጫ ሂደቱ ላይ ምንም አይነት የማታለልም ሆነ የማሰናከል ሂደት አልተፈጸመም በማለት ከደሙ ኝጹህ ነኝ ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
በርካታ የሃገሪቱ ፖለቲከኞችም የምርመራውን ውጤት ለአሜሪካ የሚበጅና መልካም አጋጣሚ በማለት ገልጸውታል።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በ2016ቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጊዜ ከሩሲያ ጋር በማበር በውጤቱ ላይ ተፅዕኖ ፈጥረዋል በሚል ወቀሳ ሲቀርብባቸው ቆይቷል።በዚሁም ሳቢያ ጉዳዩ በማስረጃ ከተረጋገጠ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሊከሰሱ ይችላሉ በሚል የሪፖርቱ ወጤት በጉጉት ሲጠበቅ ነበር።