(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 12/2011)በሚድሮክ ወርቅ ላይ ተጥሎ የነበረውን እገዳ ለማንሳት የሚያስችል ደረጃ ላይ መደረሱን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትሩ መግለጻቸው ተሰማ።
የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ባለፉት ለመገናኛ ብዙሀን ዝግ በነበረ ስብሰባ በዘርፉ ከተሰማሩ ባለሀብቶች ጋር ውይይት አድርጎ መሻሻል ስለሚገባቸው አሰራሮች ተነጋግሯል።
እገዳው የሚነሳው ሚድሮክ በአካባቢው አስከትሎታል የተባለውን ብክለት የሚያጠና የተፅዕኖ ግምገማ ቡድን ጥናቱን አጠናቆ በመጨረሱ ነው ተብሏል።
የማዕድንና ነዳጅ ሚንስትሩ ዶር ሳሙኤል ኡርቃቶ እንዳሉት በጉዳዩ ላይ የተካሄደው ሳይንሳዊ ጥናት ሚድሮክ አስከትሎታል የተባለው ጉዳት በመብት ተሟጋቾች እንደቀረበው ሳይሆን በአነስተኛ የእርምት እርምጃዎች የሚስተካከል ነው።
ድርጅቱ አሳሳቢ የሚባልና የነዋሪዎችን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥል ጉዳት ስለማድረሱ መረጃ አለመገኘቱንም ከባለሙያዎች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ሲሉ ሚንስትሩ መናገራቸውን የዋዜማ ዘገባ ያመለክታል።
ሚንስትሩ የጥናት ውጤቱን መደምደሚያ ምን እንደሆነ ከመግለጽ ተቆጥበዋል ።
ሜድሮክ ወርቅ ማዕድን ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ለሀያ አመታት በተሰጠው ፈቃድ በኦሮምያ ክልል በአዶ ሻኪሶ ወረዳ ለገደንቢ አካባቢ ሻኪሶ ከተማ አቅራቢያ ወርቅ ሲያመርት መቆየቱ ይታወሳል።
ባለፈው አመት ለተጨማሪ አስር አመታት የማምረት ፈቃዱ በወቅቱ በማዕድን ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ከታደሰለት በሁዋላ የመብት ተሟጋች ነን የሚሉ ግለሰቦች ኩባንያው ወርቅ ለማንጠር የሚጠቀምበት ኬሚካል እጅግ አካባቢን በክሏል በሚል በህዝቡ ላይ ባደረጉት ቅስቀሳ ከፍተኛ የጸጥታ ችግር መነሳቱም አይዘነጋም።
ይህን ተከትሎም ኩባንያው የታደሰለት የወርቅ ምርት ፍቃድ ታግዶ እንዲዘጋ ተደርጓል።
የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በሜድሮክ ወርቅ የብክለት ሁኔታ ላይ ዩኒቨርሲቲዎች ፣የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ፣የአካባቢ ጥበቃ ተቋማትና የውጭ ሀገራት ባለሙያዎች ተካተው ጥናት ሲያደርጉ ቆይተዋል
በሜድሮክ የወርቅ አምራች ኩባንያ ላይ በባለሙያዎች እየተደረገ ያለው ጥናት መጠናቀቁን የዋዜማ ዘገባ ያመለክታል።